2023-2024 የትምህርት አመት ስለተጠናቀቀ እንኳን ደስ አላችሁ

ጁን 13, 2024

ውድ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ ቤተሰቦች እና ሰራተኞች

ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ፣ አደረግነው! ዛሬ 2023-2024 የትምህርት አመት የመጨረሻው የትምህርት ቀን ነው። አሁን ወደ ጁን ወር መጨረሻ እየተቃረብን ስለሆነ፣ በዚህ የስፕሪንግ ወቅት በሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ከእናንተ ጋር ስላሳለፍኩት ጊዜ ጥቂት ለማንፀባረቅ እፈልጋለሁ። 

በዚህ የትምህርት አመት፣ የስቶን ሚል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሜሪካ የትምህርት ዲፓርትመንት የ 2023 ናሽናል ብሉ ሪባን ትምህርት ቤት ተብሎ ተሰይሟል፣ ይህም በዲስትሪክታችን 43ኛው ትምህርት ቤት እንዲሆን አድርጎታል። ብሔራዊ የትምህርት ቤቶች ቦርድ ማኅበር (National School Boards Association) ስለ ማህበራዊ ደህንነት ፕሮግራማችን የፈጠራ አቀራረብ እውቅና በመስጠት የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስን (MCPS) ሲልቨር ማግና ሽልማት ተሸላሚ አድርጎናል። እንደዚሁም MCPS በምርጥ የሙዚቃ ትምህርት ማህበረሰብነት NAMM ፋውንዴሽን ስያሜ አግኝቷል። የዩ.ኤስ. ኒውስ እና ወርልድ ሪፖርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከምርጥ 100 ት/ቤቶች ውስጥ ስምንት የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ዝርዝር አስቀምጧል። እና አራት የ MCPS ትምህርት ቤቶች የ 2024 የሜሪላንድ ግሪን ት/ቤቶች የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፣ ይህም የ MCPS ግሪን ትምህርት ቤቶችን አጠቃላይ ቁጥር ወደ 101 ያደርሳል ማለት ነው።

ማህበረሰባችን በአንድነት እየተሰበሰብን የምረቃ ሥነስርአቶችን፣ቀጣይ ስርዓቶችን፣ እና እውቅና የመስጠት ፕሮግራሞችን በጋራ አክብረናል። የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቶች ላይ በመገኘት የሲንየር ተማሪዎቻችንን ብሩህ ተስፋ መመስከር መቻላችንም እጅግ የሚያበረታታ ነው። የዘንድሮ ተመራቂዎች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ! ወደፊት ታላቅ ስኬት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ። 

ባለፈው ሳምንት ወደ 650 የሚጠጉ ጡረተኞችን፣ አንዳንዶቹ 25፣ 40፣ እና እንዲያውም 50 ዓመታት በላይ በሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) አገልግሎት ያበረከቱትን አክብሮት ሰጥተናቸዋል። የእነርሱ ቁርጠኝነት በዋጋ ሊተመን የማይችል ነው፣ ስለሆነም እያንዳንዳቸውን እጅግ በጣም እናመሰግናቸዋለን።

በሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) የሠመር ወቅት ማለት እቅድ የማዘጋጀት፣ እና ሙያዊ እድገት የሚዳብርበት ጊዜ ነው። ምንም እንኳን አንዳንድ የትምህርት ቤት ህንጻዎች ጸጥ ርጭ ቢሉም፣ የሠመር ፕሮግራሞችን የመደገፍ እና ለቀጣዩ የትምህርት አመት የመዘጋጀት ስራ ይቀጥላል።

ተማሪዎች በሠመር ዕረፍት ጊዜ እንዲደሰቱ፣ ከቤት ውጭ እንቅስቃሴዎችን እንዲያዘወትሩ፣ እና ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰብ ጋር ተወዳጅ ጊዜያትን እንዲያሳልፉ አበረታታለሁ። 

የትምህርት አመቱ መጠናቀቁን ስናከብር የተከናወኑትን ሥራዎች፣ ትጋቶች፣ የተገኘውን ትምህርትና እውቀት እንዲሁም እድገት በማሰብ እውቅና መስጠት አለብን። አስደናቂ አስተማሪዎቻችን፣ በትምህርት አመቱ በሙሉ ለተማሪዎች ላደረጋችሁት ትጋት እና አስተዋፆ በጣም እናመሰግናለን። ለወላጆች፣ ለቤተሰቦች እና ለማህበረሰቡ፣160,000 ተማሪዎቻችንን፣ በትምህርት ቤቶቻችን ልዩ አገልግሎት የሰጡ ቡድኖቻችንን፣ እና በሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ ካሉት 200 በላይ የህዝብ ትምህርት ቤቶች እና ፕሮግራሞችን የረዱንን ሁሉ ያለኝን ጥልቅ አድናቆትና ምስጋና አቀርባለሁ።

በጋራ፣ የተማሪዎቻችንን ህይወት እናበለጽጋለን እና ማህበረሰባችንን ለዛሬ እና ለወደፊቱ እናጠናክራለን። ስኬታማ ስለሆነው 2023-2024 የትምህርት አመት ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ! አስደሳች፣ሠላማዊ፣ እና የምትዝናኑበት ሠመር ይሁንላችሁ።

ልጆቻችንን እናገለግላለን፣

Monique T.  Felder, Ph.D. ሞኒክ ቲ ፈልደር (ዶ/ር)
Interim Superintendent of Schools የትምህርት ቤቶች ጊዜያዊ ሱፐርኢንተንደንት


ኢሜል ይላኩልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org