የትምህርት ዓመቱን በጠንካራ ሁኔታ ማጠናቀቅ፦

ስለ ቀሪው የትምህርት ዓመት አስፈላጊ መረጃ

ውድ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ቤተሰቦች

ተማሪዎቻችን የሚያውቁትን፣ የሚረዱትን እና ማድረግ የሚችሉትን የሚያሳዩ ስለሆነ የትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ግምገማዎች አስፈላጊ ናቸው። ተማሪዎቻችን የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለባቸው። የሜሪላንድ አጠቃላይ የግምገማ ፕሮግራም (ወይም "MCAP" ፈተና) በሜሪላንድ የተጠያቂነት ስርዓት ውስጥ የተንፀባረቀውን የተማሪዎች የትምህርት አፈፃፀም የሚለካበት ዋና አካል ነው። MCAP አፈፃፀም የሜሪላንድ ትምህርት ቤት የሪፖርት ካርድ ቁልፍ አካል ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የኮከብ ደረጃ አሰጣጦችን ያካትታል። ወደድንም ጠላንም፣ የተማሪዎቻችንን አፈጻጸም፣ የትምህርት ቤቶቻችንን አፈጻጸም እና በዲስትሪክታችን ያለንን አፈጻጸም የውጪው ዓለም የሚገመግመው እና የሚያየው በዚህ መንገድ ነው። 

ይህ አስፈላጊ በመሆኑ በጣም በቁም ነገር እንመለከተዋለን። ተማሪዎች የተሟላ ትምህርት፣ ትርጉም ያለው ልምምድ እና ደጋፊ ሁኔታዎችን እንደሚያገኙ ማረጋገጥ ለተማሪዎች እና ለትምህርት ቤቶች የበለጠ አዎንታዊ ውጤቶችን ለማስገኘት ይረዳል።

ስለዚህ በፈተና መርሃ ግብራችን ላይ ስለሚደረጉ ለውጦች እና ተማሪዎን ለሚመጡት የትምህርት ምዘናዎች እንዴት ማዘጋጀት እንደሚችሉ አንዳንድ ወሳኝ መረጃዎችን ለእርስዎ ለማካፈል ነው የጻፍንልዎት።

ቁልፍ መረጃዎች፦

አንዳንድ ፈተናዎች መጀመሪያ ላይ ሁሉም ትምህርቶች ከመሰጠታቸው በፊት ከስፕሪንግ እረፍት በኋላ ወዲያውኑ ለመስጠት መርሃግብር ተይዞላቸው ነበር። ይህንን ለማስተካከል፣ ፈተናውን በተቻለ መጠን ለማዘግየት በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የስቴት ፈተና መርሃ ግብራችንን እያስተካከልን ነው። አሁን ፈተና መስጠት የሚጀመረው ኤፕሪል 28 ሲሆን እስከ ሜይ ድረስ ይቀጥላል። 

ቤተሰቦች በቤት ውስጥ እንዴት መርዳት እንደሚችሉ እነሆ፡

  1. በትምህርት ላይ መገኘት (አተንዳንስ) ዋጋ አለው

    • በአሁኑ ጊዜ ተማሪዎን ለመደገፍ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ቀላል መንገዶች አንዱ፡ በየቀኑ እና በሰዓቱ ትምህርት ቤት መገኘታቸውን ያረጋግጡ።

    • በዚህ ጊዜ ጥቂት ቀናት እንኳ መቅረት ማለት ትምህርት ያመልጣቸዋል፤ ለፈተናም ዝግጅት ማጣት ሊያስከትልባቸው ይችላል። ቀጥተኛ የሆነ የትምህርት ክትትል ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀስሙ እና ለትምህርት ምዘናዎች/ግምገማዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።

  2. በመጀመሪያ፣ መሰረታዊ ነገሮች፡

    • ሠዓት ጠብቆ እንቅልፍ በጊዜ መተኛት፣ የምግብ ጊዜ መጠበቅ፣ እና የቤት ስራ የሚሠሩበትን ጊዜ ጨምሮ ተገቢ የሆነ የዕለት ተዕለት ተግባሮችን እንዲያከናውኑ ያበረታቱ።

    • በየጊዜው ወቅታዊ ድጋፎችን ለመስጠት ከተማሪዎ ትምህርት ቤት ጋር ግንኙነት ይኑርዎት።

    • አዎንታዊ አስተሳሰብን እንዲገነባ/እንድትገነባ ያጠናክሩ፤ ጥረት ማድረግና እድገት የማይነጣጠሉ አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸውን ለተማሪዎ ያስገንዝቡ።

    • በተለይ ፈተና የወስዱበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ በጥናት እና በእረፍት ጊዜ ትኩረታቸውን የሚበታትኑ ነገሮችን ይገድቡ።

  3. በቤት ውስጥ ለማጠናከር የሚረዱ ሌሎች ቁልፍ የሆኑ ስልቶች፡

    • ተማሪዎ ለጥያቄ ሲመልስ/ስትመልስ ሀሳቡ(ቧ)ን እንዲያብራራ/እንድታብራራ ይጠይቁ።

    • በጥንቃቄ ማንበብ፣ ማስረጃ መጠቀም እና ስራቸውን መፈተሽ የመሳሰሉ ስልቶችን ያጠናክሩ። 

    • ተማሪዎ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ከማድረግ ይልቅ በየቀኑ ትንሽ በትንሹ ማከናወን እንዲለማመድ/እንድትለማመድ ያበረታቱ።

    • ስህተት ሲፈፀም አንዱ የመማር አካል እንደሆነ እና አእምሮ እንዲያድግ እንደሚረዳ ለተማሪዎ ያስታውሱ።

    • ተማሪዎ ጊዜው(ዋ)ን በእርጋታ እድንዲጠቀምበት/እንድትጠቀምበት፣ በጥንቃቄ እንዲያነብ/እንድታነብ፣ እና ስራው(ዋ)ን በጥንቃቄ እንዲፈትሽ/እንድትፈትሽ ያግዙት/ያግዟት።

  4. በቤት ውስጥ ለመማር የሚደግፉ ኦንላይን ሪሶርሶች/ግብዓቶች፡

የጊዜ ሰሌዳዎችን ስናስተካክል፣ አንዳንድ ሁነቶች ሊለወጡ ስለሚችሉ በቤተሰቦች እና በትምህርት ቤቶች ፕሮግራሞች ላይ ለውጥ ሊያስከትሉ እንደሚችል እንገነዘባለን። ፈተና ስለሚሰጥባቸው ቀናት እና ሌሎች የዓመቱ መጨረሻ ዝግጅቶች ወይም ክብረ በዓላትን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን በቀጥታ ከተማሪዎ ትምህርት ቤት ይሰማሉ። 

ይህ የዓመቱ በጣም የተጨናነቀ እና አስደሳችም ጊዜ ነው። የጸደይ/የስፕሪንግ እረፍት ተቃርቧል፣ የጸደይ/የስፕሪንግ ወቅት ትምህርት ለመከታተል ስትመለሱ እርስዎ እና ቤተሰብዎ በእርፍት የታደሰ አዕምሮ እና ጉልበት ይዛችሁ እንደምትመለሱ ተስፋ እናደርጋለን!  እና በእረፍት ጊዜ ከተማሪዎ ጋር ክለሳ ለማድረግ የሚያስችልዎትን የአካዳሚክ ማጠናከሪያ ትምህርት የሚፈልጉ ከሆነ - አዘጅተናል - እባክዎን ከተማሪዎ ጋር ለመከለስ ተጨማሪ የትምህርት አይነት ሪሶርስ ለማግኘት ከፈለጉ ከላይ ያለውን አገናኝ ይጎብኙ።

መልካም የጸደይ/የስፕሪንግ ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ ከእረፍት በኋላ ተጨማሪ መረጃዎችን እናሳውቃለን።

የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ Montgomery County Public Schools


በዚህ አድራሻ ኢሜል ላኩልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org