የሞንትጎመሪ ካውንቲ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች
 

English / español / 中文 / français / Português / 한국어 / tiếng Việt / አማርኛ/Amharic

 

የትምህርት ዓመቱ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲጀመር፡ ምናልባት በዚህ የሠመር ወቅት ማንበብ ያለባችሁ በጣም አስፈላጊ መልእክት ነው

ውድ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ቤተሰቦች

የትምህርት አመቱ ሊጀመር ሁለት ሳምንት ብቻ ሲቀሩት፣ በአየሩ ላይ ብዙ ደስታ ቢኖርም፣ ነገር ግን ኃቁን መቀበል ስላለብን – ትንሽ ስጋትም ይደመጣል። ከትምህርት ቤት አቅርቦቶች፣ የጊዜ ሰሌዳዎች፣ እና የመጀመሪያ ቀን መሽቀርቀር የበለጠ አስፈላጊ የሆነው፣ ስለ ትምህርት ቤቶች ደህንነት በሁሉም አእምሮ ውስጥ የሚመላለስ ጉዳይ ነው። 

ወላጆች ብዙ ጊዜ ቀላል ጥያቄ ይጠይቁኛል፦ "ልጄ በትምህርት ቤት ውስጥ ደህንነቱ(ቷ) የተጠበቀ እንዲሆን ምን እያደረክ ነው?"

እውነታው ግን ሁልጊዜ ፍጹም የሆነ ደህንነትን የሚያረጋግጥ አንድም አይነት ፕሮግራም፣ ቴክኖሎጂ፣ ወይም አሰራር አለመኖሩ ነው። የተሻለ ነገር መኖሩን ብነግራችሁ ደስ ባለኝ ነበር። ልጆች ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንደሚሆን፣ አንድ ነገር እንደሚማሩ እና የተሻለ ልምድ እንደሚቀስሙ ይጠበቃል። እኛም የምንጠብቀው ይህንን ነው! እናም ይህ ለተወሰኑ ልጆች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም በሞንትጎመሪ ካውንቲ የሕዝብ ት/ቤቶች (MCPS) ውስጥ ለሚማሩ 155,000 ተማሪዎች እውን እንዲሆን የእናንተን እርዳታ እንፈልጋለን።

በየዓመቱ፣ የተማሪዎቻችንን እና የሰራተኞቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ የሚረዱ በርካታ የደህንነት ጥበቃ ደረጃዎችን ማጠናከራችንን እንቀጥላለን። እነዚህ በተለያየ ደረጃ የሚከናወኑ የደህንነት ጥበቃ ተግባሮች ስልጠና፣ የአደጋ ጊዜ ሂደቶችን የመከላከል ልምምድ፣ ከህግ አስከባሪ አካላት እና በመጀመሪያ ደርሰው ምላሽ ከሚሰጡት ጋር ጠንካራ ትብብር ማድረግ፣ የአእምሮ ጤና ድጋፎችን ማበረታታት፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ መገልገያዎች እና በሌሎች የትምህርት ቤት ደህንነት ጥበቃ እርምጃዎች ላይ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ማድረግን ያካትታሉ። ከሁሉም በላይ፣ ጠንካራ ግንኙነቶች ሲኖሩ ሰዎች በትምህርት ቤት ደህንነት አጠባበቅ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ይችላሉ።

በጣም ደህንነታቸው የተጠበቀ ትምህርት ቤቶች ማለት፦ ተማሪዎች የሚታመኑባቸውን አዋቂዎች ያሉበት፣ ቤተሰቦች እርስ በርስ የሚተሳሰሩባቸው፣ ሰራተኞች ከተማሪዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት የሚገነቡባቸው እና የት/ቤት ደህንነት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ሁሉም ሰው የሚረዳባቸው ቦታዎች ናቸው።

ይህ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ያለፈው የትምህርት ዓመት ሁላችንንም ያስታውሰናል። በሁለት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የጦር መሳሪያ ተኩስ ተከፍቶ እንደነበረ እናስታውሳለን። እንዲሁም መዘጋት የነበረባቸው በሮች ሳይዘጉ መቅረታቸው፣ ጎጂ የሆኑ የጥላቻ አድልዎዎችን የሚያንፀባርቅ የጥፋት መልእክቶች እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችና አስፈሪ የደህንነት ስጋቶችን አሳልፈናል። 

ምንም እንኳን እያንዳንዱን አደጋ ማስወገድ ባንችልም፣ አብረን በመስራት፣ አደጋን መከላከል እና መቀነስ እንችላለን።

ሁላችንም የደህንነት ማስከበር ሂደቶችን ስንከተል፣ ስጋቶችን ቀደም ብለን ስናሳውቅ፣ የውጪ በሮችን ዘግተን እና ቆልፈን ስንጠብቅ፣ እና ችግር ቀውስ ከመሆኑ በፊት አብረን ስንሰራ አደጋን እንከላከላለን/እንቀንሳለን። እነዚህ ደንቦች ብቻ ሳይሆኑ፤ የሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚረዱ ተግባሮች ናቸው።

የትምህርት ቀን ለመጀመር እየተዘጋጀን ሳለ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ከዚህ ጋር የተካተተውን መረጃ አንድ ላይ ለመመልከት ጥቂት ደቂቃዎችን እንዲያሳልፍ እጠይቃለሁ።

የአደጋ ጊዜ አሠራሮቻችንን ይወቁ።

እባክዎን ከልጅዎ ጋር መደበኛ የአደጋ መከላከልና ምላሽ ፕሮቶኮል (SRP) ይገምግሙ። ተማሪዎች እነዚህን የአተገባበር ሂደቶች ዓመቱን ሙሉ ይለማመዳሉ፤ ይህም በአደጋ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በትክክል እንዲያውቁ ነው። ቤተሰቦችም እነዚህን መረዳት አለባቸው። ሁሉም ሰው ምን እንደሚጠበቅበት ሲያውቅ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት የተሻለ ዝግጅት እናደርጋለን። እዚህ የበለጠ ይወቁ (ከቻሉ ይህንን ገጽ ቤትዎ ላይ ይለጥፉት)።

በግልጽ ተነጋገሩ።

ካሉን በጣም ውጤታማ ከሆኑ የደህንነት መሳሪያዎች (ምንም እንኳን አስፈላጊ ቢሆኑም) ዋነኛው ካሜራ ወይም የተቆለፈ በር አይደለም ።

ውይይት ማድረግ እና መነጋገር ነው።

እባክዎ ልጅዎ የሆነ ነገር ትክክል ካልሆነ፣ ለታመነ አዋቂ ሰው መንገር እንዳለበት ያስታውሱ። አብዛኛዎቹን ሁኔታዎች መከላከል የሚቻለው ችግሩ ከመባባሱ በፊት አንድ ሰው ከተናገረ ነው። ቤተሰቦች ስጋቶችን በቀጥታ ለትምህርት ቤታቸው ወይም ስም-ሳይገለጽ በሜሪላንድ ሴፍ ስኩልስ ቲፕ መስመር/Maryland Safe Schools Tip Line ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ። MCPS ስለ ጥላቻ/አድልዎ በሚመለከት ያሉትን ፕሮቶኮሎች የበለጠ ይወቁ። 

የተማሪዎችን የስነምግባር ደንብ ይመልከቱ።

የተማሪዎች የስነምግባር ደንብ ብዙውን ጊዜ እንደ አንድ የዲሲፕሊን ሰነድ ተደርጎ ይታሰባል። በእርግጥ አይደለም።

ይህ መከባበር የተሞላበት፣ ምቹ የሆነ፣ ሥርዓት ያለው፣ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ ትምህርት ቤቶችን መፍጠር የማህበረሰባችንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ተግባር ነው። ተማሪዎች እንዲማሩ፣ አወንታዊ ግንኙነቶችን እንዲገነቡ እና ሁሉም ሰው ደህንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ቤት አካባቢን በመጠበቅ ረገድ ሚና እንዳለው እንዲረዱ የሚያስችሏቸውን ጥረቶች ያንፀባርቃል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ከመጀመሪያው የትምህርት ቀን በፊት ስለ ትምህርት ቤቶች ደህንነት አንድ ላይ እንዲወያዩ እና እንዲገመግመው አበረታታለሁ። ተማሪዎች ለባህሪያቸው እና በዚህ ሰነድ ለተጠቀሱት ባህርያትና የስነምግባር ይዘት ተጠያቂ ይሆናሉ።
እነዚህን አገናኞች/ሊንኮች በመጠቀም የተማሪዎችን የስነምግባር ደንብ አንብቡ።

ስለ MCPS የተማሪዎች የስነምግባር ደንብ ማጠቃለያ ይመልከቱ
የተማሪዎች የስነምግባር ደንብ (2026-2027 የተሻሻለ)

የጦር መሳሪያን ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ መታወቅ አለበት።

በቤትዎ ልጆች በሚደርሱበት በማንኛውም ቦታ የጦር መሳሪያ ካለ፣ እባክዎን ጥይቱ ወጥቶ፣ መቆለፉንና እና ጥይት ካለበት ቦታ ተለይቶ ለብቻ መቀመጡን ያረጋግጡ። ይህን ማድረግ አዋቂዎች አሳዛኝ ሁኔታዎችን ለመከላከል ሊያደርጉት ከሚችሏቸው በጣም ቀላል እና ውጤታማ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው። እባክዎን ልጅዎን ማንኛውም አይነት የጦር መሳሪያ — የሚመሳሰሉ የጦር መሳሪያዎችን፣ ቢላዎችን፣ ፔፐር ስፕሬይ፣ እና ሌሎች የተከለከሉ ጎጂ ነገሮችን — ወደ ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ ይዘው መግባት እንደማይችሉ በግልፅ ይንገሯቸው። እዚህ የበለጠ ግንዛቤ ማግኘት ይችላሉ።

ማህበራዊ ሚዲያን በጥንቃቄ ይጠቀሙ።

ማህበራዊ ሚዲያ ግንኙነት ለማድረግ የሚጠቅም ቢሆንም፥ አንዳንድ ጊዜ፣ የምንለጥፈው ነገር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በእጅጉ ሊያባብሰው ይችላል። በአደጋ ጊዜ፣ ወሬዎች፣ ያልተረጋገጡ ግምቶች፣ እና ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ በፍጥነት ይሰራጫሉ። በማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚደረግ አንድ ልጥፍ ፍርሃት ሊፈጥር፣ ቤተሰቦችን ግራ ሊያጋባ፣ እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎች እና የትምህርት ቤት ሰራተኞች ስራቸውን ማከናወን እንዳይችሉ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል። ትክክለኛ መረጃ ሁልጊዜ የሚገኘው ከኦፊሴላዊ ከሞንትጎመሪ ካውንቲ የሕዝብ ት/ቤቶች (MCPS) የመገናኛ አውታሮች እና ከሕዝብ ደህንነት አጋሮቻችን የሚመጣው ነው። እባክዎን ልጅዎ በኦንላይን ይጠቀም/ትጠቀም እንደሆን ተነጋገሩበት። ከመለጠፋቸው ወይም ከማጋራታቸው በፊት በጥንቃቄ ያስቡበት። ከዚህ የበለጠ ግንዛቤ ማግኘት ይችላሉ.

ስለ አእምሮ ጤንነት ተነጋገሩ።

የትምህርት ቤት መጀመሪያ ቀን ለብዙ ተማሪዎች አስደሳች ነው፣ ነገር ግን ጭንቀት፣ ውጥረት፣ ወይም እርግጠኛ አለመሆንንም ሊያስከትል ይችላል። እባክዎን ልጅዎ የሚያስፈልገውን/የሚያስፈልጋትን እርዳታ መጠየቅ የጥንካሬ ምልክት መሆኑን አስረግጠው ይንገሩ/ያስረዱ። ከአስተማሪ፣ ከካውንስለር፣ ከስነ-ልቦና ባለሙያ፣ ወይም ከሌላ ታማኝ አዋቂ ሰው ጋር ቢነጋገሩም፣ እያንዳንዱ ተማሪ ብቻውን አለመሆኑ(ኗ)ን እንዲያውቅ/እንድታውቅ እንፈልጋለን። እዚህ የበለጠ ግንዛቤ ማግኘት ይችላሉ.

ቀኑን ሙሉ በትምህርት ቤት ሞባይል ስልኮች አይፈቀዱም።

ከዚህ የትምህርት ዓመት ጀምሮ፣ MCPS ወደ ሜሪላንድ ከስልክ-ነጻ የትምህርት ቤት ሕግ ስለተሸጋገርን በሁሉም የክፍል ደረጃዎች "No Cell, Bell to Bell"ህግ ተግባራዊ እያደረገ ነው። በጣም አስተማማኝ የሆኑ የመማሪያ አካባቢዎች ማለት፦ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች የሌሉበት እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው አካባቢዎች ናቸው። በትምህርት ቀን የግል ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እና ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን መጠቀምን መገደብ የመማር እና የትምህርት ቤት ደህንነትን ለመጠበቅ ይረዳል።
እዚህ የበለጠ ግንዛቤማግኘት ይችላሉ፦ ፖስተሩን ይመልከቱ።

እናመስግናለን

የትምህርት ቤቶቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ የእርስዎን እርዳታ እንፈልጋለን። እያንዳንዱ ወላጅ ልጃቸውን ትምህርት ቤት ሲያስረክቡ በራስ መተማመን ሊሰማቸው ይገባል። እያንዳንዱ ተማሪ ወደ ትምሕርት ቤቶቻችን በራፍ ሲደርስ ደህንነት ሊሰማው ይገባል።

ከመጀመሪያው የትምህርት ቀን በፊት ከልጅዎ ጋር (አስቀድመው) እነዚህን መገልገያዎች ለመገምገም ጥቂት ደቂቃዎችን ስለወሰዱ እና ስለ ትብብርዎ እናመሰግናለን። ሁሉም የትምህርት ቤቶቻችን ማህበረሰቦች ደህንነቱ የተጠበቀ መልካም የትምህርት ዓመት እንዲኖራቸው ለማድረግ አብረን ለመስራት በጉጉት እጠብቃለሁ።

 

Thomas W. Taylor, Ed.D., M.B.A. Superintendent of Schools
ቶማስ W. ቴይለር ዶ/ር የትምህርት ቤቶች ሱፕርኢንተንደንት
የሞንትጎመሪ ካውንቲ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች (MCPS)

 

ኢሜል ይላኩልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org