ለቀጣዩ የትምህርት አመት የስራ ማስኬጃ በጀት ቅነሳን የሚመለከት ወቅታዊ መረጃ

ከጊዚያዊ ሱፐርኢንተንደንት ዶ/ር ሞኒክ ፌልደር የተላለፈ መልእክት

ጁን 4, 2024

የተወደዳችሁ ቤተሰቦች

የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ የትምህርት ባለሙያዎች እንደመሆናችን፣ የእኛ ተልእኮ የተማሪዎቻችንን ስኬቶች ማበረታታት እና ለተማሪዎቻችን ለዕድሜ ልክ የሚጠቅማቸውን የትምህርት ልምዶችን መስጠት ነው። ይህንን ተልእኮ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣በየአመቱ ለትምህርት ስርዓታችን ፍላጎቶች ቅድሚያ ለመስጠት እንጥራለን። 

ዛሬ፣ MCPS እያጋጠመው ስላለው የበጀት ተግዳሮቶች ለእርስዎ ማሳወቅ እወዳለን። በቀደመው ለህብረተሰብ የተላከ መልዕክት ላይ እንዳጋራነው፣ በሞንትጎመሪ ካውንቲ ካውንስል የፀደቀው የመጨረሻው የባጀት ድጋፍ መጠን በ 2025 የበጀት ዓመት ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የስራ ማስኬጃ በጀት የተቀነሰ መሆኑን ያሳያል። ይህ ሁኔታ ዲስትሪክቱ መሥራት የሚፈልጋቸውን ለማሟላት ስለማያስችለን አገልግሎቶችን መቀነስ ማለት ነው።

በዚህ ምክንያት በመጪው የትምህርት አመት ከምንተገብራቸው ስልቶች አንዱ በሁሉም የመማሪያ ክፍል ከዚህ በፊት የነበረው የተማሪ ቁጥር በየክፍሉ በአንዳንድ ይጨመራል። ይህ ውሳኔ በአስተማሪዎች መካከል የነበረውን የሰራተኛ ምደባ ለውጥ ያስከትላል። ሰኞ፣ የትምህርት ቤቶች ርእሰ መምህራን በየትምህርት ቤቶቻቸው የሚኖረውን አመታዊ የሰው ሃይል ምደባ ሪፖርት ደርሷቸዋል። ይህ ሪፖርት ለቀጣዩ የትምህርት አመት ለት/ቤቶቻቸው የሚሰጠውን የመምህራን ድልድል የሚያንፀባርቅ ሲሆን በሚደረገው የሠራተኞች ቅነሳ ምክንያት ከዚህ በፊት ከነበረው የክፍል ተማሪዎች ቁጥር በየክፍሉ በአንድ ተማሪ ተጨማሪ ይደረጋል። ርእሰ መምህራን በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ሪፖርቶች እየገመገሙ እና ከማዕከላዊ ጽ/ቤት አገልግሎቶች አጋሮቻቸው ጋር እየሰሩ ያሉት ማንኛውም የመምህራን ቁጥር መቀነስ በተማሪዎች ትምህርት ላይ አነስተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ለማረጋገጥ ነው። ሌሎች የትምህርት ቤት አገልግሎቶች እንደ ካውንስለሮች፣ የትምህርት ቤት ሳይኮሎጂስቶች፣ እና የተማሪ ሰራተኛ የመሳሰሉ ሰራተኞች በእነዚህ ቅነሳዎች እንደማይነኩ መታወቅ አለበት።

በተጨማሪም የበጀት ቅነሳው በ 21 የማእከላዊ አገልግሎት ሰራተኞች ላይ ተጽእኖ አሳድሯል፣ እንዲሁም ሌሎች የባጀት አጠቃቀም ቁጠባዎችን እውን ለማድረግ በዲስትሪክቱ ውስጥ ያሉ የኮንትራት አገልግሎቶችን ተጨማሪ ቅነሳዎችን ለማድረግ መገምገማችንን እንቀጥላለን። የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) በሜሪላንድ ስቴት ውስጥ ካሉት አነስተኛ የማዕከላዊ አገልግሎት ሰጪ ካሏቸው ክፍሎች አንዱ ሲሆን ይህም የሆነው ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን ለት/ቤት ስራዎች ድጋፍ እንዲውል በማድረግ እና በሰራተኞች ምደባ ላይ ስለሚውል ነው። ቦርዱ እስከ ጁን 11 ድረስ ስለ 2025 የበጀት ዓመት የስራ ማስኬጃ በጀት የመጨረሻ እርምጃ ይወስዳል። 

ሰራተኞች እና ቤተሰቦች እነዚህ ቅነሳዎች እንደሚያሳስባቸው እናውቃለን። ነገር ግን፣ በተማሪዎች ትምህርት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቀነስ ያለንን ቁርጠኝነት ደግመን ልንገልጽ እንፈልጋለን። MCPS እጅግ በጣም ጥሩ ትምህርት እና የማስተማር አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ ነው፤ እናም ይህን የምናደርገው በትምህርት ቤቶች እና በቢሮዎች ውስጥ ከፍተኛ ብቃት ያለው የሰው ሃይል በመያዝ ነው።

ስለ ልጆቻችን ትምህርት ያለዎትን ግንዛቤ እና ስለሚያደርጉት ቀጣይ ድጋፍ እናመሰግናለን። በእኛ የጋራ ጥረት ለተማሪዎቻችን በተቻለ መጠን የተሻለ የመማሪያ አካባቢ መኖሩን እናረጋግጣለን።

ልጆቻችንን እናገለግላለን፣

Monique T. Felder Ph.D.
Interim Superintendent of Schools


ኢሜል ይላኩልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org