የሞንትጎመሪ ካውንቲ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች
 

English / español / 中文 / français / Português / 한국어 / tiếng Việt / አማርኛ/Amharic

 

ስለ ደህንነት በቤት ውስጥ መደረግ ያለበት አስፈላጊ ውይይት

የተወደዳችሁ ቤተሰቦች

ስለ አመቱ ጥሩ የትምህርት ጅምር እና የተሳካ የመጀመሪያ የውጤት መስጫ ጊዜ እናመሰግናለን። ይህ መልእክት ምንም ትርጉም የማይሰጥ ከሆነ ይቅርታ ጠይቃለሁ፤ ነገር ግን አዲሱ የማርክ መስጫ ጊዜ ለአፍታ ቆም ብለን፣ ማሰላሰል፣ ማንፀባረቅ እና በቅርብ ጊዜ የሚከናወኑ ወሳኝ ተስፋዎችን በአካዳሚክ እና የት/ቤት ደህንነትን በሚመለከት እንድናስብ ትክክለኛው ጊዜ ነው። ዛሬ ይህንን መልእክት የጻፍኩት፣ በጣም አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ላይ የእርስዎን እርዳታ ለመጠየቅ ነው።

የትምህርት ቤቶች ማህበረሰቦቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ በጋራ መስራታችንን ስንቀጥል፣ በትምህርት ቤቶቻችን እና በሰፊው ማህበረሰባችን ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ የሚያሳድር አንድ ወሳኝ ጉዳይ ማንሳት እፈልጋለሁ፤ ይኸውም ስለ ጦር መሳሪያ ደህንነት፣ ተተኳሽ መሳሪያን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስቀመጥ፣ እና በቤተሰብ ውስጥ ግልጽ ውይይት ማድረግ ነው።

የጦር መሳሪያዎችን ከወጣቶች እጅ የማራቅ አስፈላጊነት ከምንጊዜውም በላይ ግልጽ እና ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልግ ሆኗል።  እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ባለፈው የትምህርት አመት በቶማስ S. ውተን እና በጄምስ ሁበርት ብሌክ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተከሰቱትን ከባድ ሁኔታዎች በማህበረሰባችን ውስጥ በአካል አይተነዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ ከጦር መሳሪያ ጋር የተያያዙ ጉዳቶች እና የሞት አደጋዎች በህጻናት እና በታዳጊዎች (1 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉት) ዋነኛ የሞት አደጋ መንስኤ መሆኑ እንደቀጠለ ነው። ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበ አኃዛዊ መረጃ ብቻ አይደለም፤ እዚህ ሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ የሚታይ እውነታ ነው።

የትምህርት ቤት ደህንነት የጋራ ኃላፊነት ሲሆን፣ ይህም በመላው ማህበረሰባችን ንቁ ​​ትብብርና ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ነው። በቤት ውስጥ አስቀድሞ የመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ፣ ጥቃትንና በአጋጣሚ የሚፈጠሩ የአደጋ ጉዳቶችን ለመከላከል ከሚረዱ እጅግ ውጤታማ መንገዶች አንዱ ነው። የሚጠበቁ ነገሮችን በማጠናከር ረገድ በቤት ውስጥ ለማከናወን የእናንተን ያላሠለሰ ድጋፍ እፈልጋለሁ።

የእርስዎን/የእናንተን እርዳታ በእጅጉ የምፈልገው በዚህ ረገድ ነው፤ እነዚህም በእርግጥ ሕይወትን ሊታደጉ የሚችሉ ሦስት ነገሮች ናቸው፦

#1 - የጦር መሳሪያ ጥቃትን መከላከል ሁላችንንም ይመለከታል። ከልጆችዎ ጋር ስለተተኳሽ መሳሪያዎች ግልጽ እና ቁምነገር የተሞላበት ውይይት ያድርጉ፤ እንዲሁም ስለ መሳሪያዎች ተደራሽነት ወይም ተተኳሽ መሣሪያ ማግኘት ስለመቻላቸው በግልጽ ጠይቋቸው። በቤተሰብዎ ውስጥ የሚጠበቁ ነገሮችን በግልጽ ያስረዱ/ይወስኑ፤ እንዲሁም በትምህርት ቤት ውስጥ የጦር መሳሪያዎችን መያዝ የተከለከለ መሆኑን አበክረው ማስገንዘብ አለብዎት። በዚህ ዓመት ቀደም ብሎ እንደተገለጸው፣ ልጅዎ “አጠራጣሪ ነገር ካየ(ች)፣ ይናገር/ትናገር” (See Something, Say Something) የሚለውን መርህ መከተል እንዳለበ(ባ)ት ያበረታቱ፤ ማለትም፦ ትክክል ያልሆነ ነገር ካስተዋለ(ች) ለሚያምነው/ለምታምነው አዋቂ ሰው እንዲነግር/እንድትነግር፣ እንዲሁም ድጋፍ የሚያስፈልግ ከሆነ የአእምሮ ጤና እና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ አገልግሎት ክፍልን እንዲጠይቅ/እንድትጠይቅ ያበረታቱ። ጠበኝነት እና ጥቃት መፈጸም መቼም ቢሆን ተቀባይነት የለውም። 

#2 - ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን ለየብቻ፣ ተቆልፈው እና ጥይት ሳይጎርስባቸው ማስቀመጥ፤ በድንገተኛ የጦር መሳሪያ አደጋዎች የመጎዳት እድልን 85%፣ እና በጦር መሳሪያ በራስ ላይ አደጋ የማድረስ እድልን 78% ይቀንሳል።  በትክክለኛ እና አስተማማኝ በሆነ ቦታ በጥንቃቄ የማስቀመጥ ዘዴ፣ የጦር መሳሪያ ይዞ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የመገኘት እድልንም ይቀንሳል።

በቤታችሁ ውስጥ የጦር መሳሪያ ካላችሁ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ እነዚህን አስፈላጊ የደህንነት ተግባሮች እንዲከተል አጥብቄ አሳስባለሁ።

  • በጥንቃቄ እና በአስተማማኝ ሁኔታ ማስቀመጥን ተለማመዱ፦ በቤትዎ ውስጥ የጦር መሳሪያዎች ካሉ ወይም ልጅዎ መድረስና ማግኘት በሚችልበት/በምትችልበት በማንኛውም ቦታ፣ እባክዎትን መሣሪያዎቹ መቆለፋቸውን እና ከጥይት ተለይተው መቀመጣቸውን ያረጋግጡ። የጦር መሳሪያ ማስቀመጫ መቆለፊያ ያላቸው ሳጥኖችን፣ ወይም የጦር መሳሪያ መቆለፊያ ገመዶችንና የቃታ (ትሪገር) መቆለፊያዎችን መጠቀም፣ አዋቂ ሰዎች አሳዛኝ አደጋዎችን ለመከላከል ሊወስዷቸው ከሚችሏቸው እርምጃዎች መካከል ቀላሉና ውጤታማ መንገድ ነው።
  • በትምህርት ቤት የሚጠበቅ ባህሪን በግልፅ ያስቀምጡ፦ ልጅዎ፤ የጦር መሳሪያዎች፣ የጦር መሳሪያ የሚመስሉ ነገሮች፣ ቢላዎች፣ ፊት ላይ የሚረጭ መከላከያ (pepper spray) እና ሌሎች የተከለከሉ ነገሮች በትምህርት ቤት ውስጥ ይዞ መገኘት እንደማይፈቀድ እና ቦታ እንደሌላቸው በግልፅ ይንገሩ።
  • ስለ ሽጉጥ እና ተተኳሽ መሣሪያ ደህንነት ከልጆችዎ ጋር ተወያዩ፦ ልጆችዎ ሽጉጥ እና ተተኳሽ መሣሪያ ቢያዩ ምን ማድረግ እንዳለባቸው (ማለትም፦ መቆም፣ አለመንካት፣ ከቦታው መራቅ፣ እና ለአዋቂ ሰው መንገር) እንዳለባቸው፣ ከእድሜያቸው ጋር የሚመጣጠን ግልጽ ውይይት አድርጉ። በትምህርት ቤት ወይም በኢንተርኔት ላይ ስለ ተተኳሽ ጎጂ መሳሪያ የተጠቀሰ ነገር ከሰሙ ወይም መሳሪያ ካዩ፣ ወዲያውኑ ለታማኝ አዋቂ ሰው ወይም ለትምህርት ቤት አስተዳዳሪ እንዲያሳውቁ ለትላልቅ ተማሪዎችዎ ይንገሩ።
  • በሌሎች ቤቶች ስለሚገኙ የጦር መሳሪያዎች ይጠይቁ፡ ልጅዎ ወደ ጓደኛ ቤት ከመጎብኘቱ(ቷ) በፊት፣ በዚያ ቤት ውስጥ የጦር መሳሪያዎች መኖራቸውን እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ በጥንቃቄ መቀመጣቸውን ለመጠየቅ አያመንቱ።

#3 - በማህበረሰባችን ውስጥ የማይፈለጉ የጦር መሳሪያዎች መኖራቸውን ለመቀነስ እንዲረዳ፣ የሞንትጎመሪ ካውንቲ የስቴት አቃቤ ህግ ቢሮ ከአካባቢው የህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ስለ ጦር መሳሪያ 'Gun Buyback Event' ዝግጅት ያካሄዳል።

  • ቀን እና ቦታ፦ ቅዳሜ፣ ኖቨምበር 7, 2026 ከጠዋቱ 9 a.m. እስከ 1 p.m.
  • ቦታ፦ RedGate Park, 14500 Avery Road, Rockville
  • ዝርዝር መረጃ፦ የማህበረሰብ አባላት የማይፈልጓቸውን የጦር መሳሪያዎች ያለ ምንም ጥያቄ ማስረከብ ይችላሉ፣ በምላሹ የስጦታ ካርዶችን (gift cards) ማግኘት ይችላሉ። ወደ ዝግጅቱ ቦታ የሚያመጧቸው ሁሉም የጦር መሳሪያዎች ጥይት ያልጎረሱ መሆን አለባቸው፤ እንዲሁም በመኪናዎ የኋላ ክፍል (trunk) ውስጥ ማስቀመጥ እና በጥንቃቄ ማምጣት ያስፈልጋል።

በጦር መሳሪያ መልሶ መግዛት መርሃ ግብሮች ላይ መሳተፍ፣ ጥቅም ላይ የማይውሉ ወይም የማይፈለጉ መሳሪያዎችን - አደጋ ሊያስከትሉ ከሚችሉባቸው - ከቤት ውስጥ ለማስወገድ የሚያስችል ተግባራዊ እና ቀጥተኛ መንገድ ነው።

ይህንን መልእክት ለማንበብ ጊዜ ስለወሰዱ እና ይህንን አስፈላጊ ጉዳይ በሚመለከት በቤት ውስጥ ከልጆችዎ ጋር ስለሚወያዩ እናመሰግናለን። የልጆቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ እና ትምህርት ቤቶቻችንን ለሁሉም ሰው ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ምቹ አካባቢ አድርጎ ለመጠበቅ የምታሳዩት ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት ትልቅ ዋጋ አለው። ስለሚያደርጉት ድጋፍ እናመሰግናለን።

ከሠላምታ ጋር

Thomas W. Taylor, Ed.D., M.B.A. Superintendent of Schools

ቶማስ W. ቴይለር ዶ/ር., M.B.A. የት/ቤቶች ሱፐር ኢንተንደንት

 

ተጨማሪ ግብዓቶች እና ትምህርት ሰጪ ቁሳቁሶች

  • የሜሪላንድ የትምህርት ቤት ደህንነት ማዕከል፦ ለወላጆች የተዘጋጀ፤ የጦር መሳሪያ አያያዝና ጥንቃቄ መመሪያ
  • ዩ.ኤስ የትምህርት መምሪያ፦ የጦር መሳሪያን በጥንቃቄ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ስለማስቀመጥ የሚገልጽ የመረጃ ጽሑፍ
  • ChildSafe ፕሮጀክት፦ የጦር መሣሪያዎን ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማስቀመጥ እና ለልጆች ስለ የጦር መሣሪያ ደህንነት ማስረዳት
  • Everytown for Gun Safety፦ ጥንቃቄ ያድርጉ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የጦር መሣሪያ አያያዝ መመሪያ/Be SMART Secure Storage Guide
  • Sandy Hook Promise፦ Secure Storage of Lethal Means: Keeping Families Safe
  • የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፖሊስ መምሪያ፦ የጦር መሳሪያ መቆለፊያ ስርጭት እና የደህንነት ጥንቃቄ ፕሮግራሞች
 

በዚህ አድራሻ ኢሜል አድርጉልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org