የሞንትጎመሪ ካውንቲ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች
 

English / español / 中文 / français / Português / 한국어 / tiếng Việt / አማርኛ/Amharic

 

ለተማሪዎች እና ለቤተሰቦች የተላለፈ መልእክት፡ እርዳታ ለመጠየቅ የት መሄድ እንዳለብን ሁላችንም ማወቃችንን እናረጋግጥ

ውድ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ቤተሰቦች እና ተማሪዎች

የትምሕርት ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ እንደጀመራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህንን የጻፍኩበት ምክንያት በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ ስላለው ወሳኝ ጉዳይ፣ ማለትም ስለ ተማሪዎች የአእምሮ ጤና፣ አስፈላጊ መረጃ ለማካፈል ነው። ተማሪዎቻችን ብዙ ጫናዎችን ይሸከማሉ፤ እነዚህም የትምህርት ቤት ግዴታዎች፣ የጓደኝነት ግንኙነቶች፣ የቤተሰብ ተግዳሮቶች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ፣ ጭንቀት፣ የሐዘን ስሜት፣ የጉልበተኝነት ጥቃት እና የእድገት ሂደት የሚያመጣቸው ዕለታዊ ጫናዎች—በአጠቃላይ የህይወት ፈተናዎች—ናቸው። ይህ ሁሉ የሚከናወነው ደግሞ፣ ብዙ አይነት የስነ-ልቦና ጫናዎችንና ጭንቀቶችን ሊያባብሱ በሚችሉ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች በተሞላና ውስብስብ በሆነ የዲጂታል ዓለም ውስጥ ነው። በቀላል አገላለጽ፣ አንድ ተማሪ በመልክ ሲታይ ጥሩ ስለሚመስል ብቻ ሁለመናው(ዋ) ጥሩ ነው ብለን ልናስብ አንችልም። ከላይ ከሚታየው በስተጀርባ ብዙ ነገሮች እየተከናወኑ ሊሆን ይችላል።

ትኩረት መስጠት፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ እና ማዳመጥ አለብን። እኩል አስፈላጊ የሚሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ ተማሪዎች እርዳታ መጠየቅ የተለመደ ነገር መሆኑን እና በትክክል የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ የት ማግኘት እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው።

ዛሬ፣ በጋራ የኃላፊነት ስሜት ደህንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ቤት ድባብ የመፍጠርን አስፈላጊነት አጉልተን የምናንፀባርቅበት ብሔራዊ "See Something, Say Something" ቀን ነው። አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር መናገር ማለት ስለ ደህንነት ስጋትን ማሳወቅ ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት አንድ ጓደኛ ከተለመደ ባህሪው(ዋ) ወይም ስሜቱ(ቷ) ላይ ለውጥ እንዳለ አስተውሎ “ደህና ነህ(ሽ)?” ብሎ መጠየቅን ሊሆን ይችላል። እና አንዳንድ ጊዜ "የማወራው ሰው እፈልጋለሁ" ማለት ሊሆን ይችላል። 

"አንድ ነገር ካዩ ይናገሩ" 'See Something, Say Something' ማለት ለትምህርት ቤት ደህንነት እና ለተማሪዎች የአእምሮ ጤና እና ደህንነት ድጋፍ የማድረግን አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ተማሪዎቻችን ያላቸውን አማራጮችና ድጋፎች በይበልጥ እንዲያውቁ የሚያስችል ዘመቻ እያደረግን ነው። ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ፣ ተማሪዎች በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለ አእምሮ ጤና እና ደህንነት ይበልጥ ግልጽ እና ተከታታይነት ያለው መረጃ ያገኛሉ። ለምን ይህን እናደርጋለን? ምክንያቱም ብዙ መገልገያዎች/ሪሶርሶች በእጃችን ቢኖሩም፣ ሁልጊዜም በቀላሉ ሊገኙ ወይም ሊደረስባቸው በሚችል ሁኔታ አላቀረብናቸውም። ይህንን እየቀየርን ነው፤ እርዳታን በቀላሉ ማግኘት እና መጠቀም እንዲቻል እያደረግን ነው።

ይህንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ተማሪዎች በአካባቢያቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአእምሮ ጤና እና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መረጃዎችን እንዲሁም እርዳታ ለማግኘት የሚያስችሉ ግልጽ እና ቀላል መንገዶች ይኖሉ፤ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • በእያንዳንዱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች እና ኮሪደር ላይ የሚገኙ፣ ለችግር ጊዜ ድጋፍ የሚሰጡ መረጃዎችን የያዙ ፖስተሮች አሉ።
  • ተማሪዎች በቀላሉ ሊይዟቸው የሚችሉ መረጃዎችን የያዙ ካርዶች እና ስቲከሮች ይኖራሉ።
  • ሰራተኞች የሚይዟቸው ምልክቶች - ተማሪዎች እርዳታ ለማግኘት ሲፈልጉ ሊያገኟቸው የሚችሏቸውን ታማኝ አዋቂዎች እንዲለዩ ይረዳቸዋል።
  • ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የተለዩ የኢሜይል አድራሻዎች፤ ተማሪዎችን በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ካለው የድጋፍ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በቀጥታ የሚያገናኙ ናቸው።
  • በክፍል ውስጥ የሚሰጡት ትምህርቶች በአእምሮ ጤና፣ እርስ በርስ በመደጋገፍ እንዲሁም እርዳታ መቼ እና እንዴት መጠየቅ እንደሚገባ በማወቅ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ትንሽ ጠለቅ አርገን እንመልከት። እያንዳንዱ ተማሪ እና ቤተሰብ እንዲያውቋቸው በልዩ ሁኔታ የምፈልጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡-

ያን ሰው ሁን(ኚ)። ተማሪዎች እርስ በርስ እንዲተያዩ እንዲሁም እርዳታ መቼ እና እንዴት መጠየቅ እንዳለባቸው እንዲረዱ እንፈልጋለን። አንድ ተማሪ ወይም የሚያውቁት ሰው ከአእምሮ ጤና፣ ራስን የማጥፋት ሀሳብ፣ ወይም ከአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ አስቸኳይ ችግር ካጋጠመው/ካጋጠማት፣ ፈጣን ድጋፍ ለማግኘት ወደ 988 መደወል፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት መላክ፣ ወይም በኦንላይን 988 ጋር መወያየት ይችላሉ። መጠበቅ በማይችሉበት እና ወዲያውኑ እርዳታ በሚያስፈልግዎት ጊዜ ይህ ጠቃሚ ግብዓት ነው።

Here4U እያንዳንዱ ተማሪ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሊያዳምጣቸው፣ ተግዳሮቶችን እንዲወጡ ሊያግዛቸው እና አስፈላጊውን ድጋፍ ሊሰጣቸው የሚችል ታማኝ አዋቂ ሰው መለየት መቻል አለበት። ተማሪዎች የሚያናግሩት ​​ሰው ሲፈልጉ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጥ ድጋፍን ለመጠየቅ እንዲያመቻችላቸው በማድረግ፣ የበለጠ እና ግልጽ የሆነ መረጃ እየሰጠን ነው።

እገዛ ማግኘት በቀላሉ በዚህ ሊጀምር ይችላል፥ “የማወራው ሰው ፈልጋለሁ”

ያ ቀላል ሊመስል ይችላል። መሆን ያለበት፤ ዋናው ቁምነገርም እሱ ነው።
ቤተሰቦች፣ እባካችሁ ልጆቻችሁ በትምህርት ቤት ውስጥ ማንን እንደሚያምኑ እና ስለራሳቸው ወይም ስለ ጓደኛቸው የሚያሳስብ ነገር ቢገጥማቸው ለማን መንገር እንዳለባቸው ከእነሱ ጋር ተወያዩ። እርዳታ ለመጠየቅ አስቸጋሪ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ መጠበቅ እንደሌለባቸው አስታውሷቸው።

ስለዚህ ግባችን፦ ድጋፍን በቀላል ሁኔታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ በቀላሉ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ፣ እና እርዳታ መጠየቅ የተለመደ ነገር መሆኑን እንዲያውቁ ማድረግ ነው።

እኛ (MCPS) እዚህ ያለነው ለእርስዎ/ለእናንተ ነው።

Thomas W. Taylor, Ed.D., M.B.A. Superintendent of Schools
ቶማስ W. ቴይለር ዶ/ር., M.B.A. የት/ቤቶች ሱፐር ኢንተንደንት
የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ Montgomery County Public Schools


MCPS የአእምሮ ጤና አገልግሎት ድረ-ገጽ ላይ ተጨማሪ ይወቁ

ወሳኝ አገልግሎቶች፦

  • 988 ክፍት የጥሪ መስመር ነው/Lifeline
  • የሞንትጎመሪ ካውንቲ የቀውስ ማእከል (Montgomery County Crisis Center)
 

በዚህ አድራሻ ኢሜል አድርጉልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org