በሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ ለደህንነት እና ለዲሲፕሊን ያለን ቁርጠኝነት

ኤፕሪል 2024

የተወደዳችሁ ተማሪዎች፣ ሰራተኞች እና ቤተሰቦች

ሁላችሁም እንኳን ደህና መጣችሁ! ከስፕሪንግ ዕረፍት ስንመለስ፣ ትኩረት መሰጠት ያለበት ዋነኛ አንገብጋቢ ጉዳይ የእያንዳንዱን የትምህርት ቤቶቻችንን ማህበረሰብ ደህንነት መጠበቅ ነው። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ስነምግባር እየተከተሉ ቢሆንም በማህበረሰብ፣ በተማሪዎች እና በሰራተኞች መካከል በተካሄዱ ውይይቶች እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዜና ዘገባዎችም ላይ ጎልተው የሚደመጡት የተማሪዎችን ባህሪና ስነምግባር የሚመለከቱ ግንባር ቀደም ጉዳዮች ናቸው። የውይይቶቹ ትኩረት፥ በተማሪዎች መካከል የሚታየው አለመከባበር፣ የተማሪዎች ግጭቶች፣ በጉልበተኝነት ሌሎችን መጉዳት እና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያት ላይ ያነጻፀሩ ናቸው። 

ሁኔታው ወላጆችን፣ ሰራተኞችን፣ ተማሪዎችን እና ማህበረሰባችንን ያሳስባቸዋል። በእኛም በኩል አሳሳቢነቱ ግልፅ በመሆኑ፥ ከእያንዳንዱ ተማሪ የሚጠበቅበ(ባ)ትን የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ የተማሪ የስነምግባር ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን። MCPS በሥነ ምግባር ደንቡ ውስጥ የተዘረዘሩትን መርሆች ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት ጸንቶ ይቆማል፣ ይህም የተከለከሉ ባህሪያትን መፈፀም ሌሎች መዘዞችን ጭምር ሊያስከትል ይችላል። ከሰራተኞቻችን በተጨማሪ ማህበረሰባችን እና ተማሪዎቻችን የሚጠበቅባቸውን መረዳታቸው አስፈላጊ ነው። ከስፕሪንግ ዕረፍት በፊት ይህንን ከሁሉም የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች የሚጠበቅ ድርጊት መሆኑን ያሳወቅን ሲሆን፣ በተለምዶ የሚከናወን ቢሆንም፣ ከስፕሪንግ እረፍት በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከተማሪዎች እና ከሰራተኞች የሚጠበቅባቸውን ስነምግባር እና የስነምግባር ጥሰት ስለሚያስከትለው መዘዝ ጭምር እንደገና እንዲያጤኑ አሳስበናል።

MCPS የተማሪ የስነምግባር ደንብ ምንድን ነው?

በተግባር፣ MCPS የተማሪ የስነምግባር ደንብየተከለከሉ ባህሪያትን ይዘረዝራል። መልሶ የማቋቋም፣ የተሃድሶ፣ ትምህርታዊ፣ እና በፍትሃዊነት መተግበር ያለባቸው የባህሪ ጣልቃገብነት ላይ የተመሰረቱ ቅደምተከተል ውጤቶችንም ይዘረዝራል። ደንቡ የትምህርት ቤት ርእሰመምህር ከት/ቤት የማገድ እና የማባረር እርምጃዎችን መቼ መውሰድ እንዳለበት እና እንደጥፋተኝነቱ(ቷ) ክብደት መጠን መወሰድ ያለባቸውን ተገቢ እርምጃዎችም ይዘረዝራል። መሠረታዊው ነገር፦ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የመማሪያ አካባቢን ለመጠበቅ አስፈላጊ መሳሪያ በመሆኑ ይህንን ግብ ለማሳካት የተለያዩ ስልቶችን የያዘ አጠቃላይ አቀራረብ ይጠይቃል።

ነገር ግን በመሠረታዊነት የስነምግባር ደንቡ አላማ፡ ሰዎችን – ተማሪዎቻችንን፣ ሰራተኞቻችንን እና መላውን የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ደህንነት መጠበቅና መንከባከብ ነው። ተማሪዎች የስነምግባር ህግን በማክበር ረገድ፣ መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ አካታችነትና አቃፊነትን በማጎልበት ከመልካም ስነምግባር የሚጠበቁ ባህርያትን ግልጽ እናደርጋለን። የተማሪዎች የስነምግባር ደንብ ሲተገበር ተማሪዎች ድርጊታቸው በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ እንዲገነዘቡ እና ለባህሪያቸው ሃላፊነት እንዲወስዱ ያበረታታል። የተማሪ የስነምግባር መመሪያን ተግባር ላይ ስናውል፤ ለተማሪዎቻችን ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑ አስፈላጊ እና ሁሉም ሰው ዋጋ ያለው መሆኑ አወንታዊ፣ እና ምቹ የትምህርት አካባቢ እንዲኖር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናችንን ጠንካራ መልእክት እያስተላለፍን ነው።

በግልፅ ስናስቀምጥ፦ ሁሉም ተማሪዎች እና ሰራተኞች በከፍተኛ ደረጃ ማስተማር እና ለመማር እንዲችሉ ሠላም የሰፈነበት እና የባለቤትነት ስሜት የሚሰማቸው ደህንነቱ የተጠበቀ ትምህርት ቤት አስፈላጊ ነው።

የስነምግባር ደንቡን ከመተግበር ባለፈ፣ MCPS በት/ቤቶች እና ቢሮዎች ውስጥ አካላዊ እና ስሜታዊ ደህንነትን ለመጠበቅ ብዙ እርምጃዎችን ይወስዳል፦

የአካላዊ ደህንነት እርምጃዎች፦ MCPS የተለያዩ የደህንነት እርምጃዎችን ይወስዳል፣ የውጭ በሮችን መቆለፍ፣ጎብኝዎች የደህንነት ጥበቃ በሚደረግበት በር የመግባት ሂደቶችን መተግበር፣የቪዲዮ ካሜራ ክትትል ማድረግ፣ማንቂያ ደወሎች እና በሁሉም መካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተገቢ የደህንነት ሰራተኞችን ማሟላት። በቅርቡ አጥሮችን እና የመግቢያ በሮችን በማሻሻል፣በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ካሜራዎችን መትከል፣ የመማሪያ ክፍሎችን በሮች መቆለፍያ በማሻሻል ጥበቃን አጠናክረናል።

የደህንነት ጥበቃ እርምጃዎች፦ የትምህርት ቤቶችን ቅጥር ግቢ ቀጣይነት ያለው ቁጥጥር ማከናወን እና አዲስ የደህንነት ፕሮቶኮሎችን በት/ቤታችን የደህንነት ሰራተኞች አማካኝነት እንዲተገበሩ ማድረግ አላማው ለሁሉም ተማሪዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የትምህርት አካባቢ መኖሩን ለማረጋገጥ ነው። ይህም የትምህርት ቤት መፀዳጃ ክፍሎችን እና ሌሎች በደህንነት ካሜራዎች የማይሸፈኑ አካባቢዎች ላይ የሚደረግ ቀልጣፋ ክትትልን ይጨምራል።

የፖሊስ አጋርነት፦ MCPS እና የአካባቢ ህግ አስከባሪዎች ጠንካራ አጋርነት አላቸው፣ በመሆኑም ህግ አስከባሪ ሰራተኞች የደህንነት እና የአስቸኳይ ጊዜ/የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ሂደቶችን በጋራ ይገመግማሉ። በየአመቱ የድንገተኛ ጊዜ እቅዳችንን እንገመግማለን እናም ከሞንትጎመሪ ካውንቲ የማህበረሰብ ደህንነት እና የትምህርት ቤቶች ደህንነት አስተባባሪ ጋር በጋራ እንሰራለን።

አጠቃላይ ስልጠና፦ ሁሉም ሰራተኞች እና አስተዳዳሪዎች በጉልበተኝነት ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ስለማድረስ፣ ትንኮሳ፣ አድሎአዊ የጥላቻ ክስተቶች እና መለስተኛ ጥቃቶችን የሚመለከት ግንዛቤን ለማሳደግ አመታዊ ስልጠናዎች ይሰጣሉ። ይህ ስልጠና የአካታችነትን/የአቃፊነትን አስፈላጊነት፣ የመከባበር ግንኙነቶችን፣ እና ከእያንዳንዱ ሰራተኛ የሚጠበቀውን የሪፖርት አቀራረብ ሒደቶችን በጉልህ ያንፀባርቃል።

ሪፖርት ማድረጊያ ዘዴዎች፦ የቋንቋ ትርጉም አገልግሎቶችን ጨምሮ ግልጽነት እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ብልሹ ድርጊቶችን ሪፖርት የማድረግ ስርዓቶችን ኦዲት እያደረግን እና እያሻሻልን ነው።

አጋርነት፦ የደህንነት እና የአካታችነት/የአቃፊነት ጉዳዮችን እና ሌሎች የተማሪዎችን ማህበራዊ-ስሜታዊ ድጋፎችን ለመስጠት ከማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከወላጆች እና አሳዳጊዎች ጋር መተባበር አስፈላጊ ነው። በጋራ፣ ለሁሉም ተማሪዎች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ አካባቢ መፍጠር እንችላለን።

ድጋፍ የሚሰጥ ኮሙኒኬሽን፦ መረጃ ሰጪ ደብዳቤዎች እና የማህበረሰብ ስብሰባዎች በተቻለ መጠን የተረጋገጡ እና እውነተኛ መረጃዎችን የምናስተላልፍባቸው የመገናኛ ስልቶች ናቸው። የተማሪ የግል መረጃ ጥበቃ ህግ (FERPA) አብዛኛውን ጊዜ የተወሰኑ መረጃዎችን ማጋራት ይከለክላል። ይህ በተለይ ግልጽነት የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሲከሰት የሚያበሳጭ ቢሆንም፣ እነዚህ ደንቦች የሁሉም ተማሪዎች ደህንነት እና ግላዊ መረጃቸውን የመጠበቅ መብቶችን ለማስከበር በስራ ላይ የሚውሉ መሆኑን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ከባድ ክስተቶች ሲፈጠሩ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት የሚደረጉ የግንኙነት ፕሮቶኮሎችን በትክክል መተግበራቸውን የማዕከላዊ አገልግሎት ሰራተኞች በቀጣይነት ይገመግማሉ።

ለወደፊቱ፦ ተማሪዎች የት ቦታ ሆነው ቫፕ/vape እንደሚያጨሱ ለመከታተል፣ የጦር መሳሪያ ይዘው ከሆነ የሚጠቁም መሣሪያ እና የተማሪ እና የሰራተኛ መታወቂያ ግዴታን የመሳሰሉ አዳዲስ የደህንነት ጥበቃ ስርአቶችን እያጤንን ነው። እነዚህን የመሣሰሉ አጠቃላይ ዘዴዎች የደህንነት ጥበቃ ስልቶችን በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድጉ እና ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን የስነምግባር ህግ የመጣስ ክስተቶችን ሊቀንሱ ይችላሉ። 

ለስኬታማ የትምህርት ቤት ደህንነትየማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ የአካባቢ የንግድ ማህበረሰብ፣ ህግ አስከባሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ተሳትፎ ሲያደርጉ ውጤታማነቱ ይጨምራል። ወላጆች እና ተንከባካቢዎች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ የመከባበርን እሴት፣ ደግነትን እና የሃላፊነት ስሜትን በመገንባት፣ ግልጽ የሆነ የግንኙነት ልምዶችን በማጎልበት፣ ከትምህርት ቤት ህጎችና ፖሊሲዎች ጋር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ እና ተማሪዎች በቤት ውስጥ አወንታዊ ባህሪያትን እንዲገነቡ በማድረግ ለት/ቤት ማህበረሰብ አጠቃላይ የደህንነት ባህል አስተዋፅዖ ማድረግ ይችላሉ።

በትምህርት ቤትዎ ውስጥ ደህንነትን የሚመለከት ምንም አይነት ጥያቄ ካለዎት፣ እባክዎን የትምህርት ቤቱን ርእሰመምህር ያነጋግሩ።

ለትምህርት ማህበረሰባችን ደህንነቱ የተጠበቀ ምቹ የትምህርት አካባቢ ለመፍጠር ለሚያደርጉት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና ትብብር እናመሰግናለን።


ልጆችን ማገልገል፣

Monique T. Felder, Ph.D.
Interim Superintendent of Schools


ጠቃሚ መርጃዎች/ሪሶርሶች

ሌሎች አስፈላጊ ድረ ገጾች እና መርጃዎች/ሪሶርሶች


ኢሜል ያድርጉልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org