የትምህርት ቤት ደህንነት ጥበቃ ማሻሻያ

April 12, 2023

የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ስለ ትምህርት ቤቶች ደህንነት የማህበረሰብ አገልግሎት ማስታወቂያ

ለተከበራችሁ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ማህበረሰብ፦

ይህንን ደብዳቤ የምጽፈው በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ የተማሪዎቻችንን እና የሰራተኞቻችንን ደህንነት ለማረጋገጥ የወሰድናቸውን እርምጃዎች ለማሳወቅ ነው።የማህበረሰብ ደብዳቤ መልእክታችንን በማስከተል፣ ግብአቶችን በማቅረብ ረገድ፣ የሚጠበቁ ነገሮች፣ እና የማህበረሰብ ተሳትፎን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመተግበር በትጋት ስንሠራ ቆይተናል። እነዚህ ጥረቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

የማህበረሰብ እና የአጋሮቻችን ተሳትፎ
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ፌንታኒል ስለሚያስከትለው ጉዳት እና መፍትሔ በሚመለከት ሦስት ጊዜ የቤተሰቦች ውይይት መድረኮችን አካሂደናል። እንዲሁም ማርች 1 ከሁለቱ የማህበረሰብ ማውይይት ክፍለ ጊዜዎች የመጀመሪያውን በአፐር ካውንቲ የማህበረሰብ መዝናኛ ማዕከል አጠናቀናል። ሌላውን የውይይት ክፍለ ጊዜ ወደፊት ዳወን ካውንቲ ኮንሰርቲየም ውስጥ እናደርጋለን። እነዚህ ክፍለ-ጊዜዎች ከማህበረሰባችን ጋር በቀጥታ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ለማድረግ እና የደህንነት ስጋቶችን ለመፍታት በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠቃሚ ሆነዋል።

እንዲሁም ከ MCPS ሰራተኞች፣ ከተማሪዎች፣ ከወላጆች፣ ከካውንቲ የደህንነት አጋሮች እና የማህበረሰብ ቡድን ተወካዮች የተውጣጣ የትምህርት ቤት ደህንነት አማካሪ የትብብር ቡድን ፈጠርን ስለ ት/ቤቶች ደህንነት ለመወያየት የመጀመሪያ ስብሰባ አካሂደናል። በየወሩ እየተሰበሰብን ይህ ቡድን ስለ ዲስትሪክቱ ት/ቤቶች ሠላም እና ደህንነት የደህንነት ጥበቃ ዝርዝር መግለጫ ያቀርባል።

ከህግ አስከባሪ ኤጀንሲ አጋሮቻችን ጋር ትብብራችንን እንቀጥላለን። ለእያንዳንዳቸው የማህበረሰብ ተሳትፎ ኦፊሰሮች (ኃላፊዎች) እና የህግ አስከባሪ ባልደረቦቻችን ለተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች መታጠቅ ያለባቸውን የደህንነት መጥሪያ ቁልፍ ሰጥተናቸዋል። ይህ በትምህርት ክፍልም ሆነ ከትምህርት ክፍል ውጪ ባሉበት ሰዓት እንደ አስፈላጊነቱ ድንገተኛ ሁኔታዎች ሲከሰቱ በፍጥነት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ያስችላቸዋል።

ደህንነት ላይ ያተኮረ የሰራተኞች ዝግጁነት
ስለ ደህንነት እና የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ጥያቄዎችን በጥልቀት ለመረዳት እና ለመፍታት ከታቀዱት አራት የሰራተኞች ተሳትፎ ሁለቱን አካሂደናል።

በሁሉም ትምህርት ቤቶቻችን እና ቢሮዎቻችን የፀጥታና ደህንነት ጥበቃን በሚመለከት ከደህንነት ጥበቃዎች የሚጠበቅባቸውን ወጥነት ያለው የአሠራር ደረጃዎችን አዘጋጅተናል። ስልታዊ እና አስቀድሞ ጥንቃቄ በማድረግ ረገድ ንቁ ትብብር እና ችግር ለመፍታት የሚያግዝ ከትምህርት ቤት ክላስተር የጸጥታ አስተባባሪዎች፣የደህንነት ቡድኖች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር ሳምንታዊ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ አድርገናል። በተጨማሪም፣ ሁሉም በትክክል የሚሰሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በዲስትሪክቱ ውስጥ የሚገኙትን የት/ቤቶቻችን ማህበረሰብ አድራሻዎች የተመዘገቡበትን ሲስተም እየገመገምን ነው።

ጥላቻን በሚመለከት ሪፖርት የሚደረግበትን ሂደት አሻሽለናል
ስለ ዘረኝነት እና አድሏዊ የጥላቻ ክስተቶች ሪፖርት የማድረግ ሂደትን በጥልቀት ገምግመናል፣ የተለየ ቅጽ እና ተማሪዎች ለሚፈፅሟቸው የጥፋት ድርጊቶች ወደ ትምህርት ቤት ከመመለሳቸው በፊት የግዴታ የወላጅ ኮንፈረንስ መደረግ እንዳለበት ጭምር ቅጹን አሻሽለነዋል። እነዚህ ማሻሻያዎች የት/ቤቶችን ደህንነት የሚመለከቱ ክስተቶችን በሚገባ እና በተገቢው ሁኔታ ምላሽ በመስጠትና እርምጃ በመውሰድ መፈታታቸውን ያረጋግጣሉ።

የድንገተኛ ሁኔታ/አደጋ ዝግጁነት ተግባራት
በዚህ የትምህርት ዓመት፣ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ቤተሰቦች የሚሆነውን ነገር እንዲታዘቡ እና እንዲማሩ መጋበዝን ጨምሮ ቢያንስ አንድ የድንገተኛ ጊዜ ልምምድ አጠናቀዋል። በዚህ የስፕሪንግ ወቅት፣ ትምህርት ቤቶች ወላጅ እና ልጅን የማገናኘት (PCR) ልምምዶችን ጨምሮ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ላይ የማጠናከሪያ ልምምዶችን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም ተማሪዎች ለድንገተኛ አደጋ ጊዜ መዘጋጀት እንዲያስችላቸው በድንገተኛ ጊዜ ራስን የመከላከል ልምምድ እንዲያደርጉ ተደርጓል። ተማሪዎች ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች እንዲያስታውሱ በትምህርት ቤት ማስታወቂያዎች እና ቪዲዮዎች በተደጋጋሚ ይነገራቸዋል። በተጨማሪም፥ የክትትል ስርዓታችንን ለማሳደግ ከሶስት ዙር የካሜራ ተከላዎች አንዱን በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች አጠናቀናል፣ ሁለተኛው ዙር ሜይ ወር ላይ ይጠናቀቃል፥ እና የመጨረሻው የሦስተኛው ዙር ተከላዎች በዓመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል።

የደህንነት ጥበቃ ሰራተኞች መጨመር
እየጨመረ የሄደውን የሰራተኞች መቅረት ለመተካት ለሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 1.0 ቋሚ ተተኪዎችን መድበናል። ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ያለባቸው እና ጉልህ የደህንነት ፍላጎት ላላቸው ትምህርት ቤቶች ተተኪ የደህንነት ሠራተኞችን አሰማርተናል። በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ በክላስተር ከተመደቡት የማህበረሰብ ተሳትፎ ኦፊሰሮች (CEOs) በተጨማሪ፣ የደህንነት አደጋዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ረዳት የደህንነት ጥበቃ ተወርዋሪዎች እንደ አስፈላጊነቱ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው። FY2024 በጀት ዓመት የደህንነት ጥበቃ ረዳቶችን ለመጨመር 10.0 ተጨማሪ በጀት የጠይቅን ሲሆን፥ በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ ተጨማሪ የደህንነት ሰራተኞችን የማሟላት ሂደቱን እየገመገምን ነው።

ስለ ትምህርት ቤቶች የመጸዳጃ ቤቶች መሻሻል
በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የመፀዳጃ ክፍሎችን በሮች ክፍት እንዲሆኑ የሃርድዌር ተከላው ቀጥሏል፣ ከዚህ በተጨማሪ መፀዳጃ ቤቶችን ለመቆጣጠር የዲስትሪክት አቀፍ ፕሮቶኮሎችን ተግባራዊ እናደርጋለን።

የሠላምና ደህንነት ተነሳሽነት
MCPS በሚቀጥሉት ሳምንታት ሁለት አዳዲስ የደህንነት ጥበቃ እርምጃዎችን በተመረጡ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ሙከራ ያከናውናል።

Vape Detectors፡ የተወሰኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመፀዳጃ ክፍሎች ውስጥ በድብቅ የሚያጬሱትን ነገር የሚጠቁም መሣሪያ "Vape detectors" በመትከል ላይ ናቸው። እነዚህ ጠቋሚ መሣሪያዎች በመፀዳጃ ክፍሎች ውስጥ የትንፋሽ ወይም የማጨስ ሁኔታዎችን ለመለየት ይረዳሉ፣ ይህም በተማሪዎቻችን ጤንነት እና ደህንነት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ተገቢውን እርምጃ እንድንወስድ ያስችሉናል።

የተማሪ ባጆች፡- ሁለተኛው እርምጃ/ፕሮግራም የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኙበት ጊዜ እራሳቸውን ለመለየት ባጅ እንዲዲያደርጉ ማድረግ ነው። ይህ ሰራተኞቻችን እና የጸጥታ ሰራተኞቻችን በግቢው ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን በፍጥነት እንዲያውቁ እና ሌሎች ግለሰቦችን ለመለየት ይረዳቸዋል።

ጠቃሚ/አስፈላጊ ማሳሰቢያዎች
እባክዎን ከልጆችዎ ጋር ይወያዩ እና የትምህርት ቤቶችን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ያላቸውን ሚና ያሳስቧቸው፥ እነዚህን የሚጠበቅባቸውን ደንቦች መጣስ የዲሲፕሊን እርምጃ ሊያስከትል ይችላል።

  • በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ አደንዛዥ እጾች ምንም ቦታ የላቸውም እና ይዘው ከተገኙ ወደ አሉታዊ ውጤት ሊያመራ ይችላል። የሚጠቀመውን ሰው ጤና ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው የሁሉንም የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ሠላም እና ደህንነትን ያውካል/ይጎዳል። በትምህርት ቤት ንብረት ላይ አደንዛዥ እጾች እና አልኮል በፍፁም መጠቀም አይቻልም ወይም ይዘው መምጣት የለባቸውም።
  • የጦር መሳሪያ እና ግጭቶችን ከትምህርት ቤቶቻችን ማስወገድ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተን መግለጽ እንፈልጋለን። በትምህርት ቤቶቻችን የሁሉም ሰው ሠላም እና ደህንነት የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ሌሎችን ሊጎዱ የሚችሉ ማንኛውንም አይነት የአመጽ ባህሪ፣ ማስፈራሪያዎች ወይም ድርጊቶች መታገስ የለብንም።
  • በሌላ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ መገኘትና ህግን መተላለፍ አይፈቀድም። ከሌሎች ትምህርት ቤቶች የሚመጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶቻችን እንዳይገቡ በሮችን ዘግተን መጠበቅ አለብን/እንዲገቡ መፍቀድ የለብንም። ያለፍቃድ ወደ ትምህርት ቤቱ ግቢ ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎችን ነቅተን መጠበቅ አለብን። ትምህርት ቤቶቻችንን ደህንነታቸው የተጠበቀ እና አስተማማኝ ለማድረግ ይህ አስፈላጊ እርምጃ ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ላደረጉልን ድጋፍ እና ተሳትፎ ቤተሰቦችን እና የማህበረሰቡን አባላት ማመስገን እንፈልጋለን። የደህንነት ማስከበር አሰራሮቻችንን እያሻሻልን ውይይታችንን እንቀጥላለን። የትምህርት ቤቶቻችንን ደህንነት መጠበቅ የጋራ ሀላፊነታችን ነው። “አሁን ሁላችንም በአንድነት” የእኛ ቁርጠኝነት እሴት በመሆኑ የተማሪዎቻችንን እና የሰራተኞቻችንን ሠላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለን። ትምህርት ቤቶቻችን፣ ተማሪዎቻችን፣ የእኛ ኃላፊነት።

ከልብ

M. Brian Hull
Chief Operating Officer
Montgomery County Public Schools
የሞንጎመሪ ካውንቲ የሕዝብ ት/ቤቶችEmail us: ASKMCPS@mcpsmd.org

Montgomery County Public Schools