በጣም አስፈላጊ መልክት ነው
በዚህ ሳምንት መታወቅ ያለባቸው ነገሮች

ውድ የሞንትጎሞሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ቤተሰቦች እና ሰራተኞች

ይህ ሳምንት በቶማስ S. ውተን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በመላው የሞንትጎመሪ ካውንቲ አስቸጋሪ ሳምንት ነበር። በዚህም ምክንያት፣ በዚህ ሳምንት ሊታወቁ የሚገቡ ነገሮች ከሚለው ይልቅ፣ በሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ ስለ ትምህርት ቤት ደህንነት አንዳንድ መረጃዎችን፣ አስቸጋሪ ትምህርት ማግኘታችንን እና አንዳንድ ሀሳቦችን ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ።

እንደማንኛውም ሰው፣ በቅርቡ በማህበረሰባችን እና በተለይም በውተን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተፈፀመው የጥይት እኩስ ጥቃት ልቤ ተሰብሯል፣በጣም አሳዝኖኛል። ይህ አይነት ድርጊት በየትኛውም ቦታ፣ በተለይም ለትምህርት እና ለእድገት በተዘጋጀ ቦታ ላይ መፈፀም የለበትም። የልቤ ሀሳብ፣ እና የሁላችሁም ሀሳብ፣ ከቆሰለው ተማሪ፣ ከቤተሰቡ፣ ከጓደኞቹ፣ እና ከመላው የውተን ማህበረሰብ ጋር እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። የተከሰተው ነገር በሁሉም ሰው የደህንነት ስሜት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሲሆን ስለ ማህበረሰባችን እና ስለ ትምህርት ቤቶቻችን ደህንነት ሊኖረን የሚችለውን ግምት በቀጥታ የሚፈታተን ነው። በትምህርት ቤት የተከሰተ የጥይት ተኩስ ዜና ማንኛውም የትምህርት ቤት መሪ ማጋራት የማይፈልገው ክስተት ሲሆን ወላጅም መስማት የማይፈልገው ዜና ነው። ይህ ክስተት በአንድ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ በሚገኙ ማህበረሰባችን ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል። እንዲሁም እንደ ማህበረሰብ በሚገባ የተረዳነውን ከዚህ በፊት ከተከሰቱት የጥይት ተኩስ ጥቃት ክስተቶችን አሰቃቂ ስሜቶች ትውስታ እንደገና አጭሮብናል።

በዚህ ሳምንት አብዛኛውን ጊዜ በውተን ት/ቤት ተማሪዎችን፣ ሰራተኞችን፣ እና ቤተሰቦችን እያዳመጥኩ አሳልፌአለሁ። ማህበረሰቡ በፍርሃት እና በድንጋጤ ስሜት መረበሹን ተመልክቻለሁ፣ ነገር ግን እርስ በርስ በመንከባከብ ጥንካሬ እያሳየ መሆኑንም ተገንዝቤአለሁ (#WoottonStrong)። ከዚህ ሁኔታ መፈወስ ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ለእያንዳንዱ ግለሰብም የተለየ ነው። በማናኛውም ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ ያለ ማንኛውም ተማሪ ወይም ሰራተኛ ተመሳሳይ ድጋፍ የሚያስፈልገው ከሆነ፣ እባክዎ የሚታመን አዋቂ ሰው፣ ካውንስለር ወይም አስተዳዳሪ ያነጋግሩ ወይም እዚህ ሊንክ ላይ ጠቅ ያድርጉ እና እርዳታ እንደሚገኝ እናረጋግጥልዎታለን።

በዚህ ሳምንት ውተን ትምህርት ቤትን ለመደገፍ ለተሰባሰቡ ሁሉ ጥልቅ ምስጋናዬን መግለጽ እፈልጋለሁ። በቀላል አነጋገር፣ የውተን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ሰራተኞች ጀግኖች ናቸው። በከፍተኛ ጫና እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ በሙያዊ ብቃት፣ በርህራሄ፣ እና በማያወላውል ቁርጠኝነት ምላሽ ሰጥተዋል። ለራሳቸው የድጋፍ ፍላጎት ቢኖራቸውም ለተማሪዎቻቸው ባላቸው ቁርጠኝነት ምክንያት ሥራ ላይ ተገኝተዋል። በዚህ ሳምንት በጣም ከፍተኛ ጉዳት እና ድካም ደርሶባቸዋል። ትክክለኛውን የሞንትጎሞሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስን (MCPS) እሴት ስለሚወክሉ በጋራ ምስጋናችንን ልናቀርብላቸው ይገባቸዋል። በዚህ ሳምንት በተለያዩ ጊዜያት በውተን ት/ቤት ከተማሪዎቹ እና ከሠራተኞቹ ጋር በመተባበር የተሳተፉትን ወደ 100 የሚጠጉ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎንችም በጣም አመስጋኝ ነኝ - ይህ ድጋፍ ለተወሰነ ጊዜ መቀጠል ይኖርበታል። የእነርሱ መገኘት እንክብካቤ ለማድረግ፣ ለማረጋጋት እና ለፈውስ እና ለማገገም ያለንን ቁርጠኝነት ያንፀባርቃል። ይህን ድጋፍ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ እንቀጥላለን።

በተፈጠረው የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ሰኞ ዕለት እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምላሽ በመስጠት ድጋፍ ያደረጉትን የሮክቪል ከተማ የፖሊስ መምሪያ፣ የሞንትጎመሪ ካውንቲ የፖሊስ መምሪያ፣ የሞንትጎመሪ ካውንቲ የሸሪፍ ጽ/ቤት በተመሳሳይ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። የሮክቪል ከተማ ፖሊስ በቀጣይነት መገኘት ለትምህርት ቤታችን ማህበረሰብ አስፈላጊ እና የሚታይ የደህንነት ማረጋገጫ ይሆናል። 

እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ነገር ሲከሰት፣ ለተማሪዎችና ለሠራተኞች አፋጣኝ ድጋፍ መስጠት ወሳኝ ነው። በብሔራዊ ደረጃ የተካሄደ የምርምር ጥናት እንደሚያሳየው የካውንስሊንግ አገልግሎት፣ የሚታመኑ አዋቂ ሰዎች ድጋፍ እና የእኩዮች ግንኙነት አሰቃቂ ሁኔታን እንደሚቀንስ እና በተለይም በፍጥነት ሲሰጥ ለማገገም የሚረዳ መሆኑን ያረጋግጣል። ልጆችና ጎልማሶች ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ ራሳቸውን ሲያገልሉ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ከመጠን በላይ ተደጋጋሚ የስሜት መቃወስ ሲደርስባቸው ጉዳቶቹ ይባባሳሉ። ለዚህም ነው የውተን ት/ቤትን ለመክፈት ቅድሚያ የሰጠነው - እንክብካቤ፣ ግንኙነት እና መረጋጋትን ለመስጠት ነው። የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች በቦታው ላይ ካውንስለሮችን፣ የተማሪ ሰራተኞችን፣ የማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኞችን፣ የስነ-ልቦና ባለሙያዎችን እና የቤተሰብ ተሳትፎ ባለሙያዎችን ጨምሮ በቀጥታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችን፣ ሰራተኞችን እና ቤተሰቦችን በመደገፍ እየሠሩ ቆይተዋል። ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ ሰራተኞቻችን እራሳቸውን ለመርዳት ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኙ ዘግይተን መጀመር ነበረብን - ነገር ግን ይህ በዚህ ሳምንት ካገኘነው ከባድ ትምህርት አንዱ ነው። የአእምሮ ጤና ድጋፍ ማግኘት የቅንጦት ሳይሆን በጣም አስፈላጊ ነው። 

MCPS ስለ ደህንነት

ተማሪዎች የትምህርት ቤት ደህንነት የተጠበቀ ካልሆነ በስተቀር መማር አይችሉም። በዚህ ሳምንት ብዙዎቹ ልጆቻችን እንደነገሩን፣ በትምህርት ቤት ውስጥ ደህንነት ሊሰማቸው ይገባል የመጀመሪያው ኃላፊነታችን እና ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ደህንነት ነው። 

ደህንነቱ የተጠበቀ ትምህርት ቤት ማለት ምን ማለት ነው? ደህንነት ማለት ግልጽ የሆኑ የአደጋ ጊዜ መከላከል ሂደቶችን፣ ጠንካራ የደህንነት ጥበቃ እርምጃዎችን፣ ከሚታመኑ አዋቂ ሰዎች ጋር መገናኘት እና በአስቸኳይ የድጋፍ አገልግሎት ማግኘት ነው። በሞንትጎሞሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ዙሪያ፣ በርካታ የጥበቃ እርከኖችን፣ የሰለጠኑ የደህንነት ጥበቃ ሰራተኞችን፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የመግቢያ ሂደቶችን፣ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በትብብር መሥራትን፣ ክትትል የማድረግ ስርዓቶችን፣ ልምምድ የተደረገባቸው የአደጋ ጊዜ ፕሮቶኮሎችን እና ቀጣይነት ያላቸው የደህንነት አጠባበቅ ግምገማዎች እና ኦዲቶችን አሠራር እንተገብራለን። ካጋጠመን ሁኔታ በተማርነው መሰረት እነዚህን ጥረቶች እያጠናከርናቸው ነው።

እንደዚህ አይነት ነገር ዳግመኛ እንደማይከሰት ወይም ሁሉንም ነገር ለማስተካከል ፍጹም የሆነ መፍትሄ እንዳለ ብነግራችሁ ደስ ባለኝ ነበር - ነገር ግን ብቸኛ መፍትሔ ስለሌለ አልችልም።  ሆኖም ግን፣ ይህ ማለት መሞከር የለብንም ማለት አይደለም - አጥብቀን እየሞከርን/ጥረት እያደረግን ነው። እውነታው ግን 100% ውጤታማ የሆነ አንድም ስትራቴጂ የለም። የአደጋ ስጋት የሌለበት ዓለም እንደሚኖር ቃል መግባት አልችልም። ማንም አይችልም፣ ቢሆንም ግን ይህንን ቃል እገባለሁ፡- የደህንነት ጥበቃን ለማጠናከር፣ ድጋፎችን ለመጨመር፣ እና እያንዳንዱ ተማሪ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ዋጋ ያለው እና የሚገኝበትን የትምህርት ቤት አካባቢ ለመገንባት በየቀኑ መስራታችንን እንቀጥላለን።

ደህንነት የአጭር እና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን ለማግኘት ቀጣይነት ያለው የማሻሻል ጥረት መሆን አለበት። በአጭር ጊዜ ውስጥ በውተን፣ ተጨማሪ የደህንነት እና የፖሊስ አገልግሎት እንዲሁም ተጨማሪ የደህንነት ካሜራዎችን ሽፋን ማሳደግ፣ የተሻሻሉ የበር መቆለፊያዎች እና በአደጋ ጊዜ የተማሪዎችን ግንኙነት ማሻሻል ተግባራዊ ይደረጋል። በዲስትሪክቱ ውስጥ፣ ባለፈው ዓመት የተካሄዱ የትምህርት ቤት የደህንነት ኦዲቶችን በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ውስጥ ሊያስፈልጉ የሚችሉ ተጨማሪ የደህንነት እርምጃዎችን ግምገማ እየተመለከትን ነው። በተጨማሪም፣ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የአደጋ ጊዜ የደህንነት ጥበቃ ሂደቶችን እና ፕሮቶኮሎችን ይገመግማል እንዲሁም የአእምሮ ጤና ድጋፎችን ማግኘት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ያካፍላል።

ፍጹም የሆነ አንድም ስትራቴጂ እንደሌለ ቢታወቅም፣ የትምህርት ቤት ደህንነትን ስለመጠበቅ በጣም ውጤታማው መንገድ ምን እንደሆነ በወላጆች እና በሠራተኞች ብዙ ጊዜ እጠየቃለሁ። በእኔ አመለካከት እቅድ ማዘጋጀትን፣ ፖሊሲ መዘርጋትን፣ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር ያለንን ግንኙነት እና ትብብርን፣ ተማሪዎች እና ሠራተኞች የተለማመዱት የአስቸኳይ ጊዜ መከላከል ሂደቶችን፣ ክትትልን እና አዎንታዊ የትምህርት ቤት ባህልን ጨምሮ የተለያዩ ስልቶች መኖራቸው ወሳኝ ናቸው ብዬ አምናለሁ — ይህ ልንሄድበት የሚገባ ትክክለኛ መንገድ በመሆኑ MCPS ጥረት የሚያደርገውም ይህንን ነው። በፖርትፎሊዮአችን ውስጥ ካሉት በርካታ ስልቶች ውስጥ፣ በጣም ውጤታማ የሆኑት ስልቶች የሚገረሙበት ሊሆን ይችላል።

ጠንካራ እና እያደገ የመጣ የምርምር ቡድን አለ፤ በዚህም በጣም ደህንነታቸው የተጠበቀ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ከሚታመኑባቸው አዋቂዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚሰማቸው እና ደህንነት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ሁሉም ሰው የሚረዳባቸው ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሷል። በቅድሚያ ማቀድ እና አዎንታዊ ግንኙነቶችን መፍጠር ጠንካራ የመከላከያ እርምጃችን አካል ሆኖ ይቀጥላል። ከውተን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች አመራር መሪዎች ጋር ባደረግሁት ስብሰባ፣ በትምህርት ቤት ያሉ ግንኙነቶች እና የታመኑ አዋቂዎች መኖራቸው በተደጋጋሚ የተነሣ ጉዳይ ነበር (ከብዙ ጭብጦች መካከል)። ተማሪዎች የኔ የሚሉት ስሜት ባለባቸው ቦታዎች ደህንነት እንደሚሰማቸው ነግረውናል። ተማሪዎች በትምህርት ቤት የሚያምኑት አዋቂ ሰው ሲኖራቸው፣ በግልጽ ይናገራሉ። አሳሳቢ የሆነ ነገር ሲያዩ፣ መናገር አለባቸው — እና ያ መረጃ አዋቂዎች ሁኔታው ​​ከመባባሱ በፊት እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል። 

በረዥሙ አድማሳችንን አርቀን ስንመለከት፣ እነዚህ የበለጠ ጉልበታችንን እና መዋዕለ ንዋያችንን ማፍሰስ የሚገባቸው ዘርፎች ናቸው፤ ይኼውም የተማሪዎች ተሳትፎ፣ ከታመኑ አዋቂዎች ጋር አዎንታዊ ግንኙነት ማድረግ እና በትምህርት ቤት ውስጥ ተሳታፊ የመሆን ስሜትን መፍጠር ናቸው። "አንድ ነገር ካየ(ሽ)፣ ያየኸ(ሽ)ውን ነገር ተናገር(ሪ)" የተባለው መርህ – እጅግ በጣም ውድ ሳይሆን ወይም በሎጂስቲክስ ረገድ ፈታኝ ባይሆንም እጅግ በጣም ውጤታማ ነው። ይህ ከመፈክር በላይ ነው፤ ሕይወትን የሚያድን ተግባር ሊሆን ይችላል። እርግጠኛ ባይሆኑም እንኳ፣ ስጋቶችን ሪፖርት ማድረግ ለውጥ ሊያመጣ እና ዓመፅን ሊከላከል ይችላል። ተማሪዎች የክፍል ጓደኛን ትኩረት የጎደለው የሚመስል፣ የሚያስጨንቅ ነገር መስማት ወይም የማይስማማ ባህሪን የሚመለከቱ ከሆነ ለታመነ አዋቂ ሰው መነገር አለባቸው። ይህ ለመከላከል ይጠቅማል። ይህ አካሄድ በተማሪዎችና በአዋቂዎች መካከል ደህንነትን፣ የጋራ ኃላፊነትን እና መተማመንን ቅድሚያ የሚሰጥ አዎንታዊ የትምህርት ቤት ባህል መገንባትና ማዳበርን ይፈልጋል። እንዲህ አይነት መተማመን በአንድ ጀምበር ሊገነባ ስለማይችል ጊዜ ይወስዳል።

ብዙዎቹ ተማሪዎቻችን ስለ መረጃ ሪፖርት ማድረግ እና ማህበራዊ አንድምታዎች የሚሰማቸውን ስጋት አስተጋብተዋል። አስፈላጊ ከሆነ፣ ስጋቶች ሴፍ ስኩልስ ሜሪላንድ ክፍት የጥሪ መስመር 1-833-MD-B-SAFE (1-833-632-7233) ወይም safeschoolsmd.org ድረ ገጽ ወይም በመተግበሪያ ስም-ሳይገለጽ ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ። ምንም እንኳን ስጋቶችን ሪፖርት ለማድረግ ፈጣኑ እና በጣም ውጤታማው መንገድ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚገኙ ታማኝ አዋቂዎች በኩል ቢሆንም፣ ይህ ጠቃሚ ምክር ሁሉንም ትምህርት ቤቶቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ የሚረዳ ወሳኝ መረጃን ለማጋራት ውጤታማ መንገድ ነው። እባካችሁ ይህንን በቤታችሁ ውስጥ ለሚገኙ ልጆች ምን እንደሚመስል ተወያዩ። እንዲሁም ልጆች የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ከሆኑ የልጆችን የስልክ ቁጥር ፕሮግራም እንዲያደርጉ አጥብቄ እመክራለሁ።

MCPS የተለያዩ የጦር መሳሪያ መፈተሻ ሲስተሞችን እየቃኘ/እየተመለከተ መሆኑን በዜና ላይ ሰምተው ይሆናል። ይህ እውነት ነው። እኔ ጁላይ 2024 የሱፐርኢንቴንደንት ሆኜ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ስለዚህ ቴክኖሎጂ ስንመረምር ቆይተናል። በዚህ የጸደይ/የስፕሪንግ ወቅት በጥቂት ትምህርት ቤቶች አንዳንድ ቴክኖሎጂዎችን እየሞከርን ነው፣ እና የጦር መሳሪያ መያዛቸውን አስቀድሞ የሚያሳውቅ ሲስተም ካሏቸው ሌሎች በርካታ የትምህርት ቤት ዲስትሪክቶች ጋር እየተነጋገርን ነው።  ብዙ እየተማርን ነው (ግን አሁንም ብዙ መወቅ ያለብን ነገር አለ)። ለእያንዳንዱ ሲስተም አጠቃቀም ማለት ይቻላል ጥቅሞችና ጉዳቶች እንዳሉት ተምረናል፤ እነዚህ ቀላል ውሳኔዎች አይደሉም እና አንድ ነጠላ አቀራረብ ሁሉንም የደህንነት ጥያቄዎች አይፈታም። ለምሳሌ፦ የቦርሳ ፍተሻ እና ሰዎች ሲገቡ የሚደረጉ ፍተሻዎች ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ለማስፈተሽ ፈቃደኝነትን፣ ሰፊ የሰው ኃይል እና ጊዜ የሚወስዱ ናቸው። በተመሳሳይ፣ የብረት ነክ ነገር መፈተሻ ቴክኖሎጂዎች ሰፊ መሠረተ ልማትና የሰው ኃይል ያስፈልጋቸዋል። ብረት ነገር በሚገኝበት ጊዜ፣ የጦር መሳሪያም ሆነ የጦር መሳሪያ ያልሆነ ብረት ነክ ነገር፣ እና ብረት ያልሆኑ መሳሪያዎችን (እንደ ጠመንጃ በማስመሰል የተሠሩ ነገሮችን) በመለየት ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለ ደህንነት አጠባበቅ መጨመር የሚያስችሉትን መሳሪያዎች መገምገማችንን እንቀጥላለን፣ እና የምናገኘውን ጠቃሚ ነገር እና ወቅታዊ መረጃ እናጋራለን። ጥቅሞቹ እና ጉዳቶቹ እነዚህ መፍትሔዎች የተዘነጉ ናቸው ማለት አይደለም፤ ይህ ማለት በቁርጠኝነት ብዙ የማህበረሰብ ተሳትፎ ያለው ጥልቅ ግምገማ መደረግ አለበት ማለት ነው።

ስለ ሽጉጥ አያያዝና ደህንነት እና ተደራሽነት በዚህ ሊንክ ላይ ያለውን መረጃ እንድትመለከቱ አጥብቄ አሳስባችኋለሁ - ይሄ በየአመቱ በየነሐሴ ወር ለቤተሰቦች የሚላክ ማሳሰቢያ ነው። ይህ አመታዊ ማሳሰቢያ ምናልባት በእረፍት ጊዜ መጨረሻ ላይ ወደ ትምህርት ቤት የመመለስ መልዕክቶችን በሚለዋወጡበት ጊዜ ሊጠፋ ይችላል፣ ነገር ግን በዚህ ሳምንት ቤተሰቦች ሊያነቡት አስፈላጊ ነው።

ለአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎቻችን፣ ደህንነት ማለት የልጆችን ደህንነት ለመጠበቅ የታለመ የተዋቀረ፣ በቅርበት ቁጥጥር የሚደረግበት ሁኔታ ማለት ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቻችን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቻችን ሁሉ የደህንነት ፕሮቶኮሎችን ይከተላሉ፤ ይህም ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመግቢያ ሂደቶችን፣ የጎብኚዎችን ማንነት መለየት፣ እና ቀጥተኛ የአዋቂዎች ቁጥጥርን ያካትታል፣ እንዲሁም በእድሜ ላይ የተመሰረቱ የአደጋ ጊዜ ልምዶችን በመረጋጋት እና ታማኝ አዋቂዎችን በማዳመጥ የሚከናወኑ ናቸው። ትንንሾቹ ተማሪዎቻችን ሁልጊዜ እንክብካቤ፣ ጥበቃ፣ እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ሊሰማቸው ይገባል።

ተማሪዎቻችን በዚህ ሳምንት ያዩትንና የሰሙትን እያሰላሰሉ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ይህንን ነገር ወደ ጤናማ ሁኔታ ለመመለስ የእኛ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።  በቤት ውስጥ የሚደረጉ ውይይቶችን ለመደገፍ አንዳንድ ተጨማሪ ግብዓቶችን እነሆ፦

እንደዚህ አይነት ጊዜያት MCPS ከትምህርት ስርዓት በላይ መሆኑን ያስታውሱኛል — እኛ ማህበረሰብ ነን። በአንድ ትምህርት ቤት ጉዳት ሲደርስ ሁላችንም ይሰማናል። ስለዚህ ሁላችንም በአንድነት ወደፊት እንቀጥላለን። ፍጹም ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ሁሉንም አይነት ጉዳት የሚያደርሱ አደጋዎችን ለማስወገድ ዋስትና መስጠት ብችል ምኞቴ ነበር። ሁሉንም አደጋዎች ማስወገድ አንችልም፤ ሆኖም ግን፣ አደጋን መቀነስ እና ተማሪዎች አዋቂዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲተማመኑባቸው የሚያስችል አካባቢ መፍጠር እንችላለን። 

ይህ ከባድ ነበር። ረጅም መልእክት ስላስተላለፍኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ፣ ነገር ግን ብዙ መነገር ያለበት ነገር ነው። ወደፊት መጓዝ ማለት ከማህበረሰባችን ጋር ጠንካራ ግንኙነት፣ ግልጽነት፣ እና ሐቀኛ ውይይት ለማድረግ ቁርጠኝነት ማለት ነው። ግልጽ እና ወቅታዊ መረጃዎችን የማግኘት እና ጥያቄዎችን የመጠየቅ እድል ሊኖርዎት ይገባል። ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ በንቃት ምርመራ እየተካሄደ ስለሆነ ስለተፈጠረው ነገር ብዙ እየተማርን ነው። የምናውቀውን መረጃ ማጋራት፣ ምን እያደረግን እንደሆነ ማስረዳት፣ ስጋትዎን እና አስተያየቶችዎን በጥንቃቄ ማዳመጥ እና በጥያቄዎች ላይ ለመሳተፍ ተጨማሪ እድሎችን መስጠት እንቀጥላለን። መተማመን የሚገነባው በሐቀኛ ግንኙነት ሲሆን፣ ይህንን አይነት መተማመን ማጠናከር ለእኔ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነው - ጉዳዩ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላደረጋችሁልን ድጋፍ ሁሉ አመሰግናለሁ። 

Thomas W. Taylor, Ed.D., M.B.A. Superintendent of Schools
ቶማስ W. ቴይለር ዶ/ር., M.B.A. የት/ቤቶች ሱፐር ኢንተንደንት
የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ Montgomery County Public Schools


በዚህ አድራሻ ኢሜል ላኩልን፦ ASKMCPS@mcpsmd.org